Search
Close this search box.
Archives

The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles

English French German Hebrew Swedish Spanish Italian Arabic Dutch

News: ኢህአዴግ በ600 ሚሊዮን ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ!!

በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

ብያኔው ከጸና ኪሣራው በቢሊዮን ዶላር ሊደርስም ይችላል!

ኢህአዴግ ከዓለም ባንክ ያገኘውን 600 ሚሊዮን ዶላርና በተመሳሳይ ፕሮጀክት ወደፊት ሊያገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ገንዘብ በተመለከተ አደጋ ውስጥ መውደቁ ተሰማ። ኢንስፔክሽን ፓናል (Inspection Panel – IP) የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢህአዴግ የቀረበበት ውንጀላ ከተረጋገጠ የሚያጣው ገንዘብ በቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ታውቋል። ይፋ የሆነውን መረጃ አስመልክቶ ከኢህአዴግ ወገን እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም።

ግፍ የሚፈጽሙ መንግስታትን፣ በልማት ስም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ወንጀሎችን መረጃዎችን በስፍራው በመገኘትና ከመሠረቱ ዘልቆ በመግባት አደራጅቶ ተጠያቂ የሚያደርገው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል Inclusive Development International (IDI) ከሰለባዎቹ ውክልና ተሰጥቶታል። ተቋሙም በውክልናው መሰረት ለኢንስፔክሽን ፓናል በዝርዝር የሰለባዎቹን በደል በማተት አሳውቋል።

የኢህአዴግ መከላከያ ሠራዊት የሚያደርሰውን እስራት፣ ግርፋት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ከመኖሪያ ቦታ ማፈናቀል፣ የግዳጅ ሰፈራ ወዘተ በማምለጥ ወደ ኬንያ የተሰደዱ የጋምቤላ ነዋሪዎች ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጽምባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በልማት ስም ከዓለም ባንክ በሚያገኘው የዕርዳታ ገንዘብ በመሆኑ ለባንኩ በላኩት የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክተዋል።

አቤቱታውን መሠረት በማድረግ የሚደረገው ምርመራ ውጤት ይፋ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች እንደተደረገው በዕርዳታ ስም የሚገኝን ገንዘብ ኢህአዴግ ለፖለቲካ ተግባር መጠቀሙ ሲረጋገጥ፣ በመስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ ከዓለም ባንክ ተፈቅዶ የነበረው 600ሚሊዮን ዶላር ሊከለከል ይችላል፡፡

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ በሟቹ ጠ/ሚ/ርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በጋምቤላ ክልል በተለይ የተማሩ ወንዶች ላይ በማተኮር 424 ንጹሐን የአኙዋክ ተወላጆች በተገደሉበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩት ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክልሉ ሰላም የለም፡፡ በየጊዜውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱበት ቆይቷል፡፡ በተለይም ለም የሆነውን እጅግ ሰፋፊ መሬት ለውጪ ባለሃብቶች በሳንቲም በመሸጥ ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀድሞው የደርግ ዘመን ሲካሄድ ከነበረው ባለፈ መልኩ እጅግ በሚያሰቅቅ ሁኔታ በመንደር ምስረታና አስገድዶ የማስፈር ፖሊሲ ከመኖሪያ ቀዬ የማፈናቀል ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኦክላንድ ተቋም፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ … የመሳሰሉ ድርጅቶች ያወጧቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከ1998ዓም ጀምሮ የመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) በሚል በአራት ተከታታይና ሁለት ተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ የሚደረግባቸውን ፕሮግራሞች የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማሟላት ተወጥኖ የሚካሄድ ፕሮጀክት በትምህርት፣ በጤና፣ በእርሻ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በገጠር መንገድ ሥራ፣ ወዘተ መስኮች ላይ እንዲውል (PBS I, PBS I-AF (Additional Financing), PBS II, PBS 11-AF, PBS-Social Accountability Program and PBS III) በማለት በተለያዩ ደረጃዎች ለተከፋፈለው ኦፐሬሽን ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ ከ13ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛው የዓለም ባንክ ድርሻ 2ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የተቀረው በሌሎች ለጋሽ መንግሥታት እና ድርጅቶች የሚሸፈን ነው፡፡ PBS III የተሰኘውን በሦስት ንዑሳን ፕሮግራሞች የተከፋፈለውን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በአጠቃላይ የሚፈጀው 6.3ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የባንኩ ድርሻ የሆነውን 600ሚሊዮን ዶላር ቦርዱ መስከረም 5ቀን 2005ዓም አጽድቋል፡፡

በአስገድዶ ማስፈር፣ መንደር ምስረታና ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ መብቶቻቸው የተጣሱባቸው በኬንያ የሚገኙ ሦስት የአኙዋክ ስደተኞች ተወካይ ድርጅቶች በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ሌሎች የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ባንኩ ሊሰጥ የወሰነውን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ከመዋል ይልቅ ለኢህአዴግ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እየዋለ መሆኑን በመጥቀስ ለባንኩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጂም ዮንግ ኪም መስከረም 6፤ 2005ዓም ደብዳቤ ልከዋል፡፡ በጥያቄያቸውም መሠረት በዓለም ባንክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው ገንዘብ “በልማት ስም የኢትዮጵያ መንግሥት በጋምቤላ ክልል ለሚያካሂደው የመንደር ምስረታ እየዋለ ነው” በማለት ይከሳል፡፡ ሲቀጥልም የአኙዋክ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት መንደር በማፈናቀል “የተሻለ አገልግሎት ይሰጣችኋል” በማለት በግድ የማስፈር ተግባር እየተፈጸመ ሲሆን “የተባለው አገልግሎትም ሆነ ለእርሻ የሚሆን በቂ ቦታ እንዲሁም ለከብቶች የሚበቃ የግጦሽና የውሃ ቦታ የላቸውም” በማለት ሰፈራውን የተቃወሙ ሁሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡ ይህንን ግፍ የሚፈጽሙት ደግሞ የዓለም ባንክ ለመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) ስም ለልማት እንዲውል ከሚሰጠው የዕርዳታ ገንዘብ በመንግሥት ተቀጥረው ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች መሆናቸውን ገልጾዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ ከዓለም ባንክ ጋር እንዲነጋገሩላቸው Inclusive Development International (IDI) የተባለውን ድርጅት መወከላቸውን አስታውቀዋል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)

ተመሳሳይ ጉዳዮችን በዓለምአቀፍ ደረጃ በመከታተልና በማስፈጸም የታወቀው IDI በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የመልሶ ማቋቋምና ልማት ዓለምአቀፍ ባንክና (International Bank for Reconstruction and Development (IBRD)) የዓለምአቀፍ ልማት ማኅበር (International Development Association (IDA)) ሥር ለሚገኘው የኢንስፔክተር ፓናል ባለ 18ገጽ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል) ይህ የኢንስፔክተር ቡድን ከፍተኛ ሥልጣን ያለው መ/ቤት ሲሆን የዓለም ባንክ የሚሰጠውን ገንዘብ በትክክለኛ ቦታ ላይ አለመዋሉን በመጥቀስ ክስ የሚያቀርቡ ወገኖችን ጉዳይ በመከታተልና ቦታው ድረስ የራሱን ምርመራ በማካሄድ ውጤቱ ተግባራዊ እንዲሆን የባንኩን እጅ የማስጠምዘዝ ዓቅም ያለው እንደሆነ ከዚህ በፊት ያካሄዳቸው የምርመራ ውጤቶች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ የመርማሪ ቡድን የቀረበለትን አቤቱታ መቀበሉንና በጉዳዩ ላይ የማንም ተጽዕኖ የማይደረግበትን የራሱን ምርመራ እንደሚያደርግ ከትላንት በስቲያ ባወጣው ባለ 8ገጽ መግለጫ ላይ አሳውቋል፡፡ ይህ የአቤቱታ ፋይል ቁጥር የተሰጠው ጉዳይ በግልባጭ ለባንኩ ፕሬዚዳንትና ለከሳሽ ተወካይ ድርጅት (IDI) እንዲደርስ ተደርጓል፡፡(የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)

ጎልጉል የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ ባጠናከረው መረጃ መሠረት ቡድኑ ከያዝነው ዓመት የጥቅምት አጋማሽ በኋላ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ያቀናል። ቡድኑ ስደተኞቹ የሚገኙባቸውን፣ እንዲሁም ጉዳዩን በሚመለከት አስፈላጊ የሚላቸውን ቦታዎችና ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ያነጋግራል። ለስራው መሳካት የሚሆነውን ሁሉ በሚፈለግበት ቦታ በመገኘት በግንባር እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል።

በተለያየ ጊዜ ኢህአዴግ የሚፈጽመውን ግፍና በደል በማደራጀት ሥርዓቱ ላይ ከትጥቅ የጠነከረ ትግል ማካሄድ እንደሚቻል አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል:: አያይዘውም በመላው አገሪቱ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣና የመብት ጥሰት በማሰባሰብ የኢህአዴግን የገንዘብ ምንጭ የማድረቅ፣ ብሎም በእርዳታ ገንዘብ የሚገነባቸውን የአፈና ተቋማት ማስለል እንደሚቻል አስታውቀዋል። ይህንን ታላቅ ስራ የሰሩትን አካላት ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል አስፈላጊውን ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Generate with AI

AiBud WP Chat
Scroll to Top