Archives

The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles

English French German Hebrew Swedish Spanish Italian Arabic Dutch

በሚቀጥለው ወር በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉት የሴት ብሔራዊ ቡድናችን (ሉሲዎች) እየተዘጋጁ ነው

(ከቦጋለ አበበ) በ2012የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የታንዛኒያ አቻቸውን በደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ሦስት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፎ በቀጥታ የውድድሩ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎች) ለአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የሚያ ደርገውን ቅድመ ዝግጅት በተጠናከረ ሁኔታ ጀምሯል።
ሉሲዎቹ የመጨረሻውን ኢንተርናሽናል ውድድር ካደረጉ በኋላ ለረዥም ጊዜ በእረፍት ላይ የቆዩ ቢሆንም ከመስከረም ሁለት ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በሞጆ ከተማ ልምምዳቸውን ተያይዘውታል።ልምምዳቸውን በሚያደርጉበት ቦታ ተገኝተን እንዳረጋገጥነውም በአፍሪካ ዋንጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን የሚያደ ርጉት ልምምድ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።
የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት ሉሲዎቹ ከእረፍት መልስ ልዩ የአካል ብቃት ስልጠና እያደረጉ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።እንደ አሰልጣኝ አብርሃም ገለጻ፤ ተጫዋቾቹ ወደ አካል ብቃት ስልጠና የገቡት እረፍት ላይ በነበሩበት ወቅት ራስን ዝግጁ አድርጎ ያለ መቆየት ሁኔታ ስለታየባቸው ነው።
«ተጫዋቾቹ ከእረፍት መልስ ወደ ልምምድ ሲመለሱ የአካል ብቃት ፍተሻ ሲደረግላቸው ክፍተት ነበረባቸው »ያሉት አሰልጣኝ አብረሃም፤ ተጫዋቾቹን ወደ ቀድሞ ብቃታቸው ለመመ ለስም በቀን ሦስት ጊዜ የአካል ብቃት ልምምድ እንዲሰሩ እያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስታ ወቁት።ተጫዋቾቹ በሳምንት ጊዜ ውስጥም ብዙ ለውጥ ማምጣታቸውን አስረድተዋል።
የአካል ብቃት ልምምድ በልዩ መልኩ ለተጫዋቾቹ መሰጠቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የገለጹት አሰልጣኝ አብረሃም ፤በአፍሪካ ዋንጫ ቆይታቸው የሚያደርጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስቱ ቢያንስ በሁለት ቀን ልዩነት እንደሚካሄዱ ይናገራሉ።ተጫዋቾቹ ልዩ የአካል ብቃት ስልጠና መውሰዳቸውም ጨዋታዎቹን ጠንካራ ሆነው በብቃት እንዲወጡ እንደሚያ ደርጋቸው ገልጸዋል።
እንደ አሰልጣኝ አብርሃም ገለጻ በአሁኑ ወቅት የተጫዋቾቹ ብቃትና የጤንነት ሁኔታ በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አንዳንድ ተጫዋቾች መጠነኛ ጉዳት ቢኖርባቸውም ለክፋት የሚሰጥና ከጨዋታ የሚያስቀራቸው ግን አይደለም።
ሉሲዎቹ ባለፈው ዓመት አስር ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ከአምስት ሀገሮች ጋር በማድረጋቸውም በራስ መተማመናቸውና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ የመሆን አቅማቸው ዳብሯል።
በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ የውድድር መድረኮች እየጠነከሩ መጥተዋል፤ሉሲዎች በአፍሪካ ዋንጫ ጠንካራ ፉክክር ሊገጥማቸው እንደሚችል አሰልጣኙ ቢገምቱም ውድድሮቹን በድል ለመወጣት ትኩረት ሰጥተው ጠንካራ ልምምድ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።
ልምምዳቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያካሂዱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በቅርበት በመከታተል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኙም አሰልጣኝ አብርሃም ጠቅሰው፣ በሥነ ምግብና ሥነ ልቦና ባለሞያዎች የሚደረግላቸው ሳይንሳዊ ድጋፍና ክትትልም ለቡድኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ነው የሚሉት።
እንደ አሰልጣኝ አብርሃም ገለፃ ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፈው መመለስ ብቻ ሳይሆን ዋንጫውን አሸንፈው ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያ የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለመደ ድጋፉን ለቡድኑ በመስጠት ሉሲዎቹ እ.አ.አ በ2004 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው አራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ካስመዘገቡት የአራተኛነት ደረጃ የተሻለ ውጤት ይዘው እንዲመለሱ ከጎናቸው እንዲሆን አሰልጣኝ አብረሃም ጥሪ አቅርበዋል።
«በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ቀላል አይደለም፤በምድብ ጨዋታችን የምንገጥማቸው ሀገሮች ጠንካራና በአፍሪካ ዋንጫ ትልቅ ስም ያላቸው ናቸው፤ጠንካራ ልምምድ ማድረግ ይጠበቅብናል»ያለችው የቡድኑ አምበልና የመሃል ተጫዋች ብዙሃን እንዳለ፣ ሉሲዎች ተጋጣሚዎቻቸውን በጥሩ ብቃት ተጫውተው ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ጠንካራ ልምምድ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጻለች።
እንደ ብዙሃን ገለፃ፤ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለመስራት ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ ነው፤የቡድኑ አሰልጣኞችም ተጫዋቾቹን ብቁ ለማድረግ በቀን ሦስት ጊዜ ስልጠና እየሰጡ ነው፤ ተጫዋቾችም በጥሩ መንፈስና በሞራል ጠንክረው እየሰሩ ነው።
«ዓላማችን በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ነው»ያለችው ብዙሃን፤ ቡድኑ ጠንክሮ በመስራት ጥሩ ውጤት አስመዝግቦ በዓለም ዋንጫ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለውም አስረ ድታለች።
የተጫዋቾቹ የሥነልቦና ዝግጅትና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ያላቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ እንደሆነም አመልክታለች። የተጫዋቾቹ የእ ርስ በርስ ግንኙነትና ከአሰልጣኞች ጋር ያላቸው መግባባት ለቡድኑ ጠንካራ ሥራ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለም ነው የገለ ጸችው።
«እርስ በርስ እየተያየን ጉድለቶቻችንን ለመሙላት እንጥራለን፤በቡድናችን ውስጥ ፍቅርና መደጋገፍ አለ፤አሰልጣኞቻችን እንደ ጓደኛም ይመክሩናል፤በመነጋገር ስለሚያምኑም ችግሮቻችንን በግልጽ ለመፍታት የቻሉትን ያደርጋሉ»በማለትም በቡድኑ ስላለው ሁኔታ ገልጻለች።
« ከእዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ያስመዘገበችው ከፍተኛ ውጤት አራተኛ ደረጃ ነው።ይሁን እንጂ የአሁኑ የቡድን ስብስብ ከቀድሞው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ አዲስ ታሪክ የማጻፍ ፍላጎት አለው»ያለችው ብዙሃን ለእዚህም የሕዝቡ ድጋፍ ቡድኑን ከማነቃቃት አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውና ሕዝቡ የተለመደውን ድጋፉን አሁንም እንዲያጠናክር ብዙሃን ጥሪዋን አስተላልፋለች።
እ.አ.አ ከፊታችን ጥቅምት ሃያ ስምንት እስከ ኅዳር አስራ አንድ በኢኳቶሪያል ጊኒ አዘጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ሉሲዎቹ ጠንካራ ከሚባሉት ናይጄሪያ፣ካሜሩንና ኮትዲቯር በምድብ ሁለት ተደልድለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top