Happy Ending! – ድሮግባ ቻይና ገባ

45 mins read


(ዘ-ሐበሻ) የቸልሲው ፊት አውራሪ አጥቂ ዲድየር ድሮግባ ክለቡን ለቆ ለቻይናው ሻንጋይ ሻንዋ ክለብ ፈረመ። በ24 ሚሊዮን ፓውንድ ቸልሲን በ2004 የተቀላቀለው ድርጎባ ላለፉት 8 ዓመታት በስታንፎርድ ብሪጅ የተለያዩ ድሎችን አጣጥሟል።
የቻይናው ሻንጋይ ሻንዋ የቀድሞው የቸልሲ አጥቂ ኒካላስ አኔልካም የሚጫወትበት ሲሆን አሁን ደግሞ ድርጎባ ተቀላቅሎታል። ድሮግባ ይህን ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ የመጀመሪያውን ጨዋታውን ጅላይ 25/2012 ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያደርጋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ለፕሪሲዝን ዝግጅት ኤሽያ ይዞራል።

ውድ አንባቢያን በመዲና ጋዜጣ ላይ ድርጎባ ቸልሲን ከመልቀቁ አስቀድሞ “Happy Ending!” (የድሮግባ መንገዶች) የሚል ጽሁፍ አስነብበን ነበር። ጽሁፉን አሁን በድረ ገጻችን ላይ ብታነቡት ስለአይቬሪኮስታዊው አጥቂ ጥልቅ ግንዛቤን ይሰጣችኋል ብለን ስላሰብን እንደወረደ አቅርበነዋል።

ቼልሲ የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ በብሪታኒያ ምድር ደስታው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በባየር ሙኒክ ላይ ለተቀዳጀው ከፍተኛ ድል ትልቅ አስተዋፅኦ በማበርከት የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ደግሞ ዲዲዬ ድሮግባ ነው፡፡ አይቮሪኮስታዊው ኮከብ በስታምፎርድ ብሪጅ ቆይታው ከዚህ ቀደም በቻምፒዮንስ ሊጉ ሶስት ጊዜ ለግማሽ ፍፃሜ ሲደርስ አንድ ጊዜ ደግሞ ለፍፃሜ መቅረብ ችሏል፡፡ አንድ ጊዜም እንዲሁ ሩብ ፍፃሜ ድረስ ተጉዟል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አምስት ጊዜ ሞክሮ ያልተሳካለትን ዋንጫ ማሳካት ችሏል፡፡ በእሱ ከፍተኛ ጥረትም ሰማያዊዎቹ ዋንጫውን ከፍ አድርገው ማንሳት ችለዋል፡፡

Didier Drogba’s Chelsea record
•Debut: v Manchester United, 15 August, 2004
•First goal: v Crystal Palace, 24 August, 2004
•Appearances: 342
•Goals: 157
•Honours: Premier League: 2004-05, 2005-06, 2009-10; FA Cup: 2006-07, 2008-09, 2009-10, 2011-12; League Cup: 2004-05, 2006-07 Champions League: 2011-12
•Premier League top goalscorer: 2007, 2010

በሙኒኩ አልያንዝ አሬና በተካሄደው የዘንድሮው ሲዝን የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ድሮግባ ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በግሩም ሁኔታ የአቻነቷን ጎል በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ይህም የሮቤርቶ ዲሚቲዎችንና የልጆቻቸውን የሜዳ ላይ ህይወት ያራዘመች ሆናለች፡፡ አሸናፊውን ለመለየት የሚያስችለው የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥም የመጨረሻዋንና ወሳኟን ጎል ከመረብ በማሳረፍ ታሪኩን በወርቃማ ቀለም ለመፃፍ ችሏል፡፡
የአይቮሪኮስቱ ኮከብ ብዙ ጊዜ በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የፍፁም ቅጣት ምት ገድ የለውም፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ ተቀይሮ ታሪክ መስራት ችሏል፡፡ በባህሪው ሳቢያ ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍልም ይታይ ነበር፡፡ በ2008 ፍፃሜ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ በመውጣቱ ሰማያዊዎቹን ለሽንፈት ዳርጓቸዋል፡፡ በአወዛጋቢ ሁኔታ በባርሴሎና ተሸንፈው ከውድድር በወጡበት የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታም በተመሳሳይ መልኩ በካሜራ ፊት የሰራው ብልግና አይረሳም፡፡ ከሊቨርፑል ጋር በመለያ ምት ተሸንፈው ከውድድር በወጡበት ዓመትም እንዲሁ ፔናሊቲ በመሳት ዋጋ አስከፍሏቸው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግን አሁን ታሪክ ሆነዋል፡፡ እሱም በመልካም ጎኑ ታሪክ መስራቱን ቀጥሏል፡፡
አጥቂው በማይዋዥቅ አቋሙ የምዕራብ ለንደኑን ክለብ በመጥቀም ላይ ይገኛል፡፡ በቼልሲ ማሊያ ለፍፃሜ በቀረበባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ጎሎችን ማስቆጠሩም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው የሚሆነው፡፡ ከእግርኳሰ አንፃር ካየነው እድሜው ገፍቷል ሊባል ቢችልም እሱ ግን ገና እንደ አፍላ ጎረምሳ አሁንም በጥሩ አቋም ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ለዚህም የረዳው ጠንካራ ልምምድ መስራቱና በፀሎት የተጋ ሰው መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡
በአሊያንዝ አሬና የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ድሮግባ የሰራውን ገድል ቢቢሲ የገለፀው ‹‹አጨራረሱ በሚያምር ልብ ሰቃይ ቴአትር ላይ የተሳተፈ ዋና ገፀ ባህሪ ይመስል ነበር›› በማለት ነበር፡፡ በዚህ ወሳኝ የፍፃሜ ጨዋታ አስገራሚ የጭንቅላት ኳስ በማስቆጠር ሰማያዊዎቹን ለአቻነት ሲያበቃቸው የመጨረሻዋን ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምትም ወደጎልነት በመቀየር ቼልሲን በ107 ዓመት ታሪኩ የመጀመሪያው የሆነለትን የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን እንዲስም አስችሎታል፡፡ የዝውውር መስኮቱ ሊከፈት መቃረቡን ተከትሎ በእሱ ዙሪያም የተለያዩ ወሬዎች እየተናፈሱ ይገኛሉ፡፡ ያቺ የፍፁም ቅጣት ምትም በቼልሲ ማሊያ የመጨረሻ ኳስና ጎሉ እንደሆነችም ተወርቶበታል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበለት ተጨዋቹም ‹‹ለወደፊቱ ብዙ ራዕይ ያለኝ ሰው እንደሆንኩ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜም አብዝቼ እፀልያለሁ፡፡ ወደዚህች ምድር ስመጣ የተፃፈልኝ የራሴ የሆነ ራዕይ አለኝ፡፡ ይህ ቡድን አስገራሚ ቡድን ነው፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ ስላደረገልኝ ሁሉ አመሰግነዋለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ስለቀጣይ የኳስ ህይወቴ ምንም ማለት አልችልም›› የሚል የተድፈነፈነ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ዲዲዬ ድሮግባ በቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ጎል በማስቆጠር እንግዳ አይደለም፡፡ የመጀመሪያ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታውን ያደረገው በሴፕቴምበር 2003 የማርሴይ ተጨዋች በነበረበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ በሪያል ማድሪድ 4ለ2 በተሸነፉበት በዚህ የመጀመሪያ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታው ጎል ማስቆጠር ችሎ ነበር፡፡ በድምሩም እስከዛሬ ድረስ 75 የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን አድርጎ 39 ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ በመጨረሻ የወርቅ ሜዳሊያውንም በአንገቱ አጥልቋል፡፡ በቀድሞው አሰልጣኝ አንድሬ ቪያስ ቦአስ ጊዜ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን ክለቡን ለመልቀቅ ተቃርቦ ነበር፡፡ አሁን እዛ ውሳኔ ላይ ባለመድረሱ በበጎ መልኩ ነው የሚያየው፡፡ አሁን ግን ከክለቡ መለያየቱ የተቃረበ ይመስላል፡፡
የ34 ዓመቱ አይቮሪኮስታዊ አጥቂ በስታምፎርድ ብሪጅ ለስምንት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በመውጫው በር ላይ ቆሟል፡፡ ምንም እንኳን ክለቡ አሁን አጥብቆ የሚፈልገው ቢሆንም እሱ ግን ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ አዲስ ህይወት ለመጀመር እንደሚፈልግ የቅርብ ሰዎች በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተከላካይና የአሁኑ የሰንደርላንድ አሰልጣኝ ስቲቭ ብሩስ ተጨዋቹን በተመለከተ ሰሞኑን ለቢቢሲ ሬዲዮ ፋይቭ ላይ አስተያታቸውን ሲሰጡ ‹‹ዲዲዬ ድሮግባ ላለፉት ስምንት ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ አጥቂ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን የዘንድሮው የውድድር ዓመት የመጨረሻ የፕሪሚየር ሊግ ቆይታው ይመስለኛል፡፡ ቢሆንም ግን አሁን ባለው አቋም የትም ሄዶ በድንቅ ብቃቱ መጫወት ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ቼልሲዎች ትክክለኛውን የእሱን ምትክ ያገኛሉ ወይ? የሚለው ነው›› በማለት ስለድንቅ ብቃቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የቡድን ጓደኛው ፍራንክ ላምፓርድ በበኩሉ ‹‹እሱ እውነተኛ ጀግና ነው›› ሲል አድናቆቱን ችሮታል፡፡ በ2006 እና በ2009 የዓመቱ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ለመመረጥ የበቃው ዲዲዬ ድሮግባ ከሜዳ ውጪ ያለው ህይወቱም በስኬት የተሞላ ነው፡፡ በምግባረ ሰናይ ስራዎች ላይ በሰፊው የሚሳተፍ ሲሆን 11 አባላት ያሉት የአይቮሪኮስት የእውነት አፈላላጊና እርቅ ኮሚ ሽን አባል ነው፡፡ በቀጣይ ህይወቱስ ምን ይገጥመው ይሆን?
Happy Ending!
አይቮሪኮስታዊው ከከብ ዲዲዬ ድሮግባ በቼልስ መውጫ በር ላይ ቆሟል፡፡ ይህ ለበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ለማመን የሚያስቸግር ነገር ቢሆንም እሱ ግን በአቋሙ እንደሚፀና በግልፅ ተናግሯል፡፡ አሁን የሚጠበቀው ነገር ቀጣይ ማረፊያው የት ይሆናል? የሚለው ብቻ ነው፡፡
የአፍሪካዊው ጀግና በስምንት ዓመት የስታምፎርድ ብሪጅ ቆይታው ሶስት የፕሪሚየር ሊግ፣ ሁለት የካርሊንግ ካፕ፣ አራት የኤፍ.ኤ ካፕ እና እንዲሁም አሁን በስተመጨረሻ አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ በድምሩ አስር ዋንጫዎችን ለመሳም ችሏል፡፡ ለእሱ ታላቅ ዝና መቀዳጀት የዦዜ ሞውሪኖ ሚና በእጅጉ ላቅ ያለ ነው፡፡ በ2004 ከፈረንሳዩ ማርሴይ ክለብ በ24 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ቼልሲ ያመጡትም እሳቸው ናቸው፡፡ የፖርቹጋላዊውን አሰልጣኝ ስንብት ተከትሎ እሱም ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልግ በወቅቱ ገልፆ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በኋላ ላይም በውሳኔው መፀፀቱን በመግለፅ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ሰውዬው ባለውለታው ናቸውና ይሄንን ቢያደርግ ማን ሊፈርድበት ይችላል? አሁን ግን ያን ጊዜ የተናገረውን ተግባራዊ በማድረግ ሰማያዊውን ማሊያ ለማውለቅ ከጫፍ ደርሷል፡፡
የድሮግባ መልቀቅ የምዕራብ ለንደኑን ክለብ በእጅጉ እንደሚጎዳው እሙን ነው፡፡ ጉዳዩን ዘግይቶ ቢያሳውቅም ውስጥ ውስጡን ግን አስቀድሞ ሲወራ ቆይቷል፡፡ እሱ ራሱም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደ ሌላ ክለብ በመሄድ አዲስ ህይወት ለመጀመር እንደሚችል በይፋ አስታውቋል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ወሳኟን የአቻነት እና የአሸናፊነት የፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ ካሳረፈ በኋላ ሜዳው መሀል ቆሞ ሁለት እጆቹን በማውለብለብ ለደጋፊያቸው ሰላምታ ማቅረቡም ለስንብቱ ፍንጭ የሰጠበት ሂደት እንደሆነ ተናግሮለታል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ለእሱ የተለየ ፍቅር ያላቸው አድናቂዎቹ የሆኑ የተወሰኑ የቼልሲ ደጋፊዎች አይናቸው በእምባ ሲሞላ ማስተዋሉን የዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ዘጋቢ ተናግሯል፡፡ በእርግጥም በዛ ጨዋታ ሰማያዊዎቹን ከሞት ታድጎ ታሪካዊ አድርጓቸዋልና የልብ አፍቃሪዎቹ ይሄንን ስሜት ቢያሳይ ምንም ላይገርም ይችላል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ የድል ባለቤት ለመሆን መቻሉ ብቻ ሳይሆን በ2008 ሞስኮ ላይ በዚሁ ውድድር ፍፃሜ ላይ የቀይ ካርድ ሰለባ በመሆን ቡድኑን ላስከፈለው መስዋዕትነትም አስፈላጊውን ካሳ መክፈሉን ማረጋገጡ ብቻውን የደስታውን ጥግ ከፍ ሊያደርገው ችሏል፡፡
ለመሆኑ በድሮግባ መልቀቅ ቼልሲ ውስጥ ማን ተጠቃሚ ይሆን? ብዙዎቹ ጣታቸውን በመቀሰር ላይ ያሉት ወደፈርናንዶ ቶሬስ ነው፡፡ ስፔናዊው አጥቂ በ50 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ከሊቨርፑል ወደ ቼልሲ ከተዘዋወረበት ጊዜ አንስቶ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ መሆን አለመቻሉ ድብርት ውስጥ ከትቶት ቆይቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ቤንች ላይ ለመቀመጥ መገደዱ በራሱ የፈጠረበት ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር ቆይቷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመጪው ክረምት የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት ሊሸጥ እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል፡፡ አሁን ግን የድሮግባ መሄድ እርግጥ ከሆነ እሱ በስታምፎርድ ብሪጅ እንደሚቀየርና የአይቮሪኮስታዊውን ሚና እንደሚወጣ በመነገር ላይ ነው፡፡ ቶሬስ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን አጋማሽ ደካማ አጀማመር ቢያሳይም በኋላ ላይ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየትና ጎል ማስቆጠርም ጀምሯል፡፡ በመሆኑም ድሮግባ መልቀቁ እርግጥ የሚሆን ከሆነ እሱ በስታምፎርድ ብሪጅ በመቆየት የእሱን ቦታ እንደሚተካ እርግጥ ይሆናል የሚሉ አስተያየቶች መደመጥ ጀምረዋል፡፡
የድሮግባ መውጣትና መውረድ
በ2004/05 የውድድር ዘመን 16 ጎሎችን ከመረብ በማሳረፍ ቼልሲ ከ50 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ረድቶታል፡፡ በካርሊንግ ካፑ ፍፃሜም ኳስና መረብን ማገናኘት ችሏል፡፡ በ2006/07 በአንድ የውድድር ዓመት 30 ጎሎችን በማስቆጠር ከኬሪ ዲክሰን በመቀጠል የመጀመሪያው የቼልሲ ተጨዋች ለመሆን ችሏል፡፡ በካርሊንግ ካፕ ፍፃሜ አርሴናልን ሲያሸንፉ ሁለት እንዲሁም በኤፍኤካፕ ማንቸስተር ዩናይትድን በመርታት የድል ባለቤት ሲሆኑ እንዲሁ አንድ ጎል ከመረብ አሳርፏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓመቱ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠውም በዚህ ዓመት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በ2007/08 የሆዜ ሞውሪንሆ ስንብት ተከትሎ እሱም ክለቡን የመልቀቅ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን መፀጸቱን በመግለፅ ክለቡን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በካርሊንግ ካፕ ቼልሲ በቶተንሀም ቢሸነፍም እሱ ግን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡ በዛ ሲዝን በማንቸስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ኔማንያ ቪዲችን በክርኑ በመማታቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቀ ድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ራፋ ቤኒቴዝ በበኩላቸው ሆን ብሎ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ይወድቃል በማለት ት ችታቸውን ሰንዝረውበት ነበር፡፡ በፍፁም ቅጣት ምት በማንቸ ስተር ዩናይትድ ተረትተው የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ባጡበት ጨዋታ በቀይ ካርድ መሰናበቱም ሌላው ተጠቃሽ ነገር ነው፡፡
በ2008/09 በበርንሌይ በተሸነፉበት የካርሊግ ካፕ ጨዋታ በተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ላይ ሳንቲም በመወርወሩ የሶስት ጨዋታዎች ቅጣት ሊጣልበት ችሏል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊጉ በባርሴሎና ተሸንፈው ከውድድሩ በወጡበት ግጥሚያ በካሜራ እይታ ውስት ሊገባ ችሏል፡፡
በ2009/10 ከቼልሲ ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በግሉም በ29 ጎሎች ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ጨርሷል፡፡
በ2010/11 በወባ በሽታ መጠቃቱ ቢገለፅም በቶሎ ሊያገግም ችሏል፡፡ በሀገሩ አይቮሪኮስት የተቀሰቀሰው የርስ በርስ ጦርነት አብቅቶ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የተጫወተውን ከፍተኛ ሚና ተከትሎ በታይም መፅሔት ምርጫ ከዓለማችን 10 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዱ አድርጎ ሊያካትተው ችሏል፡፡
በ2011/12 በዌምብሌይ በተካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ጎል አስቆጠረ፡፡ በፍፃሜውም እንዲሁ ሊቨርፑል ላይ ጎል አገባ፡፡ በዚህም በአራት ኤፍ.ኤ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ ጎል በማስቆጠር የመጀመሪያው ተጨዋች ለመሆን በቅቷል፡፡ S

Leave a Reply

Your email address will not be published.