Menu
Dark
Light
Today: December 22, 2024

(zehabesha.com) የልብ ህመም ጠቋሚ ምልክቶች

January 22, 2012

ብዙዎቻችን የልብ ህመም የበሽታ ምልክቶች ምን እንደሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች (ከሚዲያ፣ ከመፃህፍት፣ ወዘተ…) ተረድተን ይሆናል፡፡ ይሁንና፣ ልባችን ችግር ውስጥ መሆኑን ቀደም ሲል የማስጠንቂያ መልዕክት የሚያስተላልፉ ሌሎች ምልክቶች ቢኖሩስ?
በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች የህመሙ ተጠቂዎች ከልብ ህመም ጋር ከመጋፈጣቸው ከወራት ወይም ከዓመታት በፊት ሊያጋጥሟቸው በሚችሉ የበሽታ ምልክቶች ዙሪያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል፡፡ በኒው ጀርሲ፣ ኒዎርክ በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ህክምና ማዕከል የልብ ሐኪሙ ጆናታን ጎልድስቴይን፣ ‹‹ልባችንን ደም ከሚሰጡት ደም ቅዳዎቹ ጋር እንደ አንድ ትልቅ ጡንቻ ልንወስደው እንችላለን፡፡ ይኸው ጡንቻ መዳከም ሲጀምር የበሽታው ምልክቶች በበርካታ የሰውነታችን ክፍሎች መታየት ይጀምራሉ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ልባችንን መመርመር እንዳለብን የሚጠቁሙ አምስት ነጥቦች ከዚህ በታች ተቀምጠዋል፡፡ ከነኚህ የበሽታ ምልክቶች መካከል አንዱ፣ በተለይም የሁለት ወይም ከዚያ በላይ ምልክቶች፣ መታየት የልብ ህክምና ምርመራ ማድረግ እንዳለብን ጠቋሚ ነው፡፡
1. የአንገት ህመም
የአንገታችን ጡንቻ የተሸማቀቀ ሆኖ ተሰምቶን ያውቃል? ይህ አይነቱ ስሜት በቀላሉ ወዲያውኑ ካልጠፋ ችግር እንዳለ መጠራጠር አለብን፡፡ አንዳንድ ህሙማን የልብ ድካም ካጋጠማቸው በኋላ አንገታቸውን እንደሚያማቸውና እንደተወጠረ ይሰማቸዋል፤ ይህን የበሽታ ምልክት በወቅቱ የሚያያይዙት ከጡንቻ መዛል ጋር ነው፡፡ ሰዎች ይህን የበሽታ ምልክት ብዙ ጊዜ የሚስቱት የልብ ህመም መገለጫ አድርገው የሚወስዱት አጣዳፊ የደረት፣ የትኩሳትና የእጅ ህመምንና መደንዘዝን በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ሴቶች የልብ ህመም በዚህ መልኩ ሊሰማቸውና ከትከሻቸው ወደ አንገታቸው የሚወርድ ህመምና የጡንቻ መወጠር ከወንዶች የበለጠ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል Take charge:- A woman’s guide to a healthier Heart መጽሐፍ ደራሲና በኒው ጀርሲ ሴቶች ልብ ህመም ማዕከል ነርስ የሆኑት ማርጂ ላትሬላ ይናገራሉ፡፡ የሕመም ስሜቱ በሰውነታችን ግራ ክፍል በትከሻችንና እጃችን ዙሪያም ሊሰማን ይችላል፡፡
መንስኤ፡- ከተጎዳው የልብ ህብረ-ህዋስ የሚመነጩ የነርቭ ቃጫዎች በአንገትና በትከሻ ውስጥ ከሚገኙ የነርቭ ስሮች ጋር በመጣመር በአከርካሪያችን ወደ ላይና ወደ ታች የህመም ምልክቶችን ይልካሉ፡፡
መገለጫ፡- የህመም ስሜቱ በአንድ የተወሰነ የሰውነታችን ክፍል የሚገኝ ሳይሆን መስመር ተከትሎ የሚሰራጭ ይመስላል፡፡ የህመም ስሜቱ ላይዩላይ በረዶ ወይም ሙቀት በማድረግ፣ አሊያም ጡንቻን በማሸት አይጠፋም፡፡
2. የወሲብ ችግር
የልብ ወይም ቧንቧ ህመም ባለባቸው ወንዶች ዘንድ የብልት አለመቆም ወይም የቆመ ብልት በአጭር ጊዜ መሟሸሽ (ስንፈተ ወሲብ) የተለመደ ችግር ቢሆንም፣ እነኚህ ሰዎች በህመሙና በችግሩ መካከል ያለውን ግንኙነት ግምት ውስጥ አያስገቡትም፡፡ ለልብ ወይም ቧንቧ ህመም ህክምና በሚከታተሉ አውሮፓውያን ወንዶች ዙሪያ የተካሄደ አንድ ጥናት ከሶስት ህሙማን መካከል ሁለቱ የልብ ችግር እንዳለባቸው በህክምና ምርመምራ ከመረጋገጡ በፊት ለወራት ወይም ለዓመታት ለሚቆጠር ጊዜ የስንፈተ ወሲብ ችግር እንዳጋጠማቸው ደርሶበታል፡፡ በስንፈተ ወሲብና በልብ ወይም ቧንቧ ህመም መካከል ባለው ግንኙት ዙሪያ በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች በጣም አሳማኝ ከመሆናቸው የተነሳ ሐኪሞች የስንፈተ ወሲብ ችግር ያለው ወንድ እነሱ ዘንድ ሲመጣ የልብ ወደም ቧንቧ ምርመራ ያደርጉለታል፡፡ እንደ የልብ ሐኪሙ ጎልድስቴይን አባባል፣ ‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የስንፈተ ወሲብ ችግር ባለባቸው ወንዶች ዘንድ የልብ ድካምና የሞት አደጋው ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያሳይ ግልፅ ማስረጃ ብቅ እያለ ነው፡፡››
መንስዔ፡- በልብ ዙሪያ ያሉ ደም ቅዳዎች ሊጠቡና ሊደድሩ እንደሚችሉ ከወንዱ ብልት ጋር የሚገናኙ ደም ስሮችን በተመሳሳይ መልኩ ሲጠቡና ሊደድሩ ይችላሉ፡፡ እነኚህ ደም ስሮች አነስ ያሉ በመሆናቸው ደግሞ ፈጠን ብለው ሊጎዱ ይችላሉ፤ የልብ ህመም መኖሩ በህክምና ምርመራ ከመረጋገጡ በፊት ከሶስት እስከ አራት ዓመታት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የብልታችን ደም ስሮች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የችግሩ መነሻ ምን እንደሆነ ወዲያውኑ አይታወቅም፡፡ ማንኛችንም ብንሆን የስንፈተ ወሲብ ችግር ካጋጠመን፣ አሊያም ፍቅረኛችን ወይም የትዳር አጋራችን በዚህ ረገድ ከተቸገረ፣ የልብ ወደም ቧንቧ ህመም መኖር አለመኖሩን ለማጣራት ሐኪም ማማከር ይኖርብናል፡፡ የልብ ሐኪሙ ጎልድስቴይን፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ስንፈተ-ወሲብ ችግር ያለበት ሰው ከዚህ በተቃራኒው እስካልተረጋገጠ ድረስ የልብ ወደም ቧንቧ ህመምተኛ ተደርጎ ይወሰዳል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
3. ጭው ማለት፣ ነፍስን መሳት ወይም የትንፋሽ ማጠር
Circulation:- Joumal of the American Heart Association ላይ በወጣ አንድ ጥናት መሰረት፣ በምርመራ ሂደቱ ከታቀፉ ሴቶች መካከል ከ410 በመቶ በላይ የሚሆኑት የልብ ድካም ካጋጠማቸው ከጥቂት ቀናት በፊት ትንፋሽ ማጠር እንደደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡ በከፍታ ቦታ ላይ ስንገኝ የሚያጋጥመን አይነት የትንፋሽ ማጠር፣ ጭው ማለት ወይም ህሊና መሳት ጋር ልንፋጠጥ እንችላለን፡፡ ደረጃ ስንወጣ፣ ቤት ስናፀዳ፣ በጓሮ አትክልታችን አረም ስናርም፣ አሊያም ከዚያ ቀደም ስናከናውናቸው ምንም አይነት ችግር በማይፈጥሩብን እንቅስቃሴዎች ወቅት የትንፋሽ ማጠር ካጋጠመን፣ ነገሮችን በንቃት መከታተል ይኖብናል፡፡
መንስኤ፡- ይህ ችግር የሚፈጠረው ወደ ልባችን በቂ ኦክሲጂን ለማድረስ የሚችል ደም በደም ስራችን ውስጥ ሳይገባ ሲቀር ነው፡፡ ልባችን በቂ ደም ሳያገኝ ሲቀርም እንዲሁ አየር ወደ ውስጥ ስንስብ የህመም ስሜት ሊሰማን ይችላል፡፡ በደም ቅዳ ውስጥ በሚፈጠር ግግር ሳቢያ ለልባችን ደም የሚያቀብሉ ደም ቅዳዎች ሲዘጉ ልባችን በቂ ኦክሲጂን አያገኝም፡፡
መገለጫ፡- የትንፋሽ ማጠሩ በሳንባ ህመም ሳቢያ ከመጣ፣ ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው የሳንባችን ህብረ ህዋሳት ሲጋራ በማጨስና በሌሎች አካባቢያዊ ምክንያቶች ቀስ በቀስ እየተጎዱ ሲሄዱ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ መንስኤው የልብ ወይም የልብ ወደም ቧንቧ ህመም ከሆነ ደግሞ ትንፋሽ ማጠሩ ሲደክመን በድንገት ሊያጋጥመንና ዐረፍ ስንል ሊጠፋ ይችላል የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የሆድ መጎርበጥ ወይም የምግብ መመረዝ ጋር በተያያዘ ከተለመደው የረዥም ጊዜ ህመም ይልቅ የህመም ስሜቱ ብቅ እያለ የሚጠፋ ነው፡፡
የልብ ህመምን የሚከላከሉ ምግቦች
በእርግጥ፣ የልብ ህመም በዘር የሚተላለፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ እንደ አመጋገብ ስልትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመሰሉ የአኗኗር ምርጫዎች የልብ ህመምን በመከላከሉና በማስቀረቱ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ አምስት የምግብ አይነቶች የልብ ህመምንና ለዚህ የሚያጋልጡ ነገሮችን የሚከላከሉ አልሚ ምግቦችን በብዛት የያዙ ናቸው፡፡ እነኚህን የምግብ አይነቶች በእጃችን ይዘናቸው በቀላሉ ከቦታ ቦታ መዘዋወር ስለምንልችልም በስራ ተወጥረንም ቢሆን ልንመገባቸው እንችላለን፡፡
1. ፖም
ምናልባት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ስለሚገኝ ይሆናል፣ ፖም የሚገባውን ያህል ትኩረት ያገኘ ፍራፍሬ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ፣ ፖም ወይም ቱፋህ የልብ ህመምን በመከላከሉ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ፖም ብዙ ጊዜ በልብ ጤንነት ዙሪያ የሚካሄዱ ጥናቶች ላይ በስፋት መጠቀሱ ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ፖም በሰውነታችን ያለውን ጎጂ oxidant የሚያስወግድ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ ፍራፍሬ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ለልብ ወደም ቧንቧ ስርዓት የተለያዩ ጥቅሞችን በሚሰጠው ፔክቲን የተባለ አሰር የተሞላ ነው፡፡
የመከላከል ባህርይ፡- ኩዌርሴቲንና ሌሎች የፖም anti-oxidant ንጥረ ነገሮች በስብ ክምችት ሳቢያ የሚፈጠረውን የደም ቅዳ ምላሽ (atherosclerosis) እና ሌሎች የልብ ወይም ወደም ቧንቧ ስርዓት ችግሮችን የሚያስከትለውን የoxidative ውጥረትን ይከላከላሉ፡፡ ፔክቲን የተባለው አሰር ደግሞ ለልብ ህመም አስተዋፅኦ የሚያደርገውን ኮሌስቴሮል እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ የፖም ፀረ ብግነት ባህርይ ደግሞ አጠቃላይ የደም ስር ጤንነት ያሻሽላል፡፡
አመጋገብ፡- ሁሉም የፖም አይነቶች የልብ በሽታን የሚከላከሉ አልሚ ምግቦች አሏቸው፡፡ ከሁሉም የበለጠ የ anti-oxidant አቅም ያለው ግን ቀዩ ፖም ነው፡፡
2. ሽንብራ
ጆኒ ቦወደን The 150 Healthiest Foods on Earth መጽሐፋቸው ላይ እንደ ምስር፣ ሽንብራ፣ አተርና ባቄላ የመሰሉ ጥራጥሬዎችን በየጊዜው መመገቡ የልብ ህመም ተጋላጭነትን 22 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል በ10,000 ወንዶችና ሴቶች ዙሪያ የተካሄደ አንድ ጥናት ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡
የመከላከል ባህርይ፡- ማንኛውም ጥራጥሬ ለጥሩ የልብ ጤንነት አስፈላጊ ቢሆንም፣ የልብ ህመም ተጋላጭነትን በመቀነሱ ረገድ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው ሽንብራ ነው፡፡ ሽንብራ የኮሌስትሮል መጠንን በመቀነሱ እገዛ በሚያደርግ ሟሚ አሰር የተሞላ ብቻ ሳይሆን ልብን ከበሽታ የሚከላከሉ anti-ixidants፣ ፖታሲየምና ስብማ ኦሜጋ-3 አሲድ አለው፡፡
አመጋገብ፡- በሳምንት አራት ጊዜ ሽንብራ መመገቡ ማለፊያ ነው፡፡
3. ለውዝ
በምግብና በበሽታ መካከል ያለውን ግንኙነት ከተከታተሉ አራት ጥናቶች የተገኘውን ውህብ ያነፃፀሩ ተመራማሪዎች በየጊዜው ለውዝ መመገብ የልብ ህመም ተጋላጭነትን 37 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ደርሰውበታል፡፡ በለውዝ ውስጥ ያለው የካሎሪ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የልብ ህመምን የሚከላከሉ አልሚ ምግቦችን በብዛት የያዘ ነው፡፡
የመከላከል ባህርይ፡- ለውዝ ለልብ ጤንነት ተስማሚ የሆኑ አሰር፣ ቪታሚን ኢ፣ ፖታሲየምና ማግኒዚየም ጨምሮ በርካታ አልሚ ምግቦችን የያዘ ነው፡፡ ማግኒዚየም ለማስወጣት አስፈላጊ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ለውዝ በበርካታ ጥናቶች ከአነስተኛ የልብ ህመም ተጋላጭነት ጋር በተያያዘው የስብ አይነት (monounsaturated fat) የበለፀገ ነው፡፡
አመጋገብ፡- ጥሬ ለውዝ፣ አሊያም አንድ ሾርባ ማንኪያ ስኳር የሌለበትን የለውዝ ቅቤ ፖም ላይ ቀብቶ መብላት ጤናማ ልብ እንዲኖረን በሳምንት አራት ጊዜ ለውዝ መመገቡ ማለፊያ ነው፡፡
4. ወተት የሌለበት (ጥቁር) ቸኮላት
ኮሎምቢያዊው ሳይንቲስት ኦስካር ፍራንኮና የተመራማሪዎች ቡድናቸው በ2004 (እ.ኤ.አ) British Medical Joumal ላይ የልብ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዝ ተፈጥሯዊ የአመጋገብ ስልት አቅርበው ነበር፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፣ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱትን ሰባት የምግብ ዓይነቶች በየቀኑ መመገቡ የልብ ህመም ተጋላጭነትን እስከ 75 በመቶ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ከእነኚህ 7 የምግብ አይነቶች አንዱ የሆነው ወተት የሌለበት (ጥቁር) ቸኮላት ብቻውን የልብ ወደም ቧንቧ ስርዓት በሽታ ተጋላጭነትን 21 በመቶ መቀነስ እንደሚችል ታውቋል፡፡
የመከላከል ባህርይ፡- ጥቁር ቸኮላት ከፍተኛ የኮኮዋ መጠን አለው፡፡ ኮኮዋ ደግሞ የተደፈኑ ደም ቅዳዎችን ለመከላከል በሚያግዘው ፍላቫኖል ንጥረ ነገር የተሞላ ነው፤ በዚህም የልብ ድካምና የደም መርጋት በሽታን ይከላከላል፡፡ ጥቁር ቸኮላት የደም ግፊትን እንደሚቀንስም ተደርሶበታል፡፡
አመጋገብ፡- አነስተኛ የጥቁር ቸከላት መጠን መመገብ ለአብዛኞቻችን ለጤና ተስማሚ ነው፡፡ ሁለት የቸኮላት ቁራጮች (ከ30 ግራም በታች) በየቀኑ መመገቡ በቂ ነው፡፡
5. ወይን
ወይን ቪታሚን ሲ፣ ቪታሚን ቢ6፣ ፖታሲየምና ፍላቮኖይድ ጨምሮ የልብ ህመምን በሚከላከሉ የተለያዩ አልሚ ምግቦች የበለፀገ ነው፡፡
የመከላከል ባህርይ፡- ወይን የልብ ወደም ቧንቧ ስርዓት ጤንነትን የሚደግፈው በanti-oxidant እና ፀረ ብግነት ባህርዩ አማካኝነት ነው፡፡ በወይን ውስጥ የሚገኙ አልሚ ምግቦች በጋራ የደም ግፊትንና ኮሌስቴሮልን ይቀንሳሉ፣ እንዲሁም ልባችን በደም ስሮች በኩል ደምን እንዲያስወጣ ያግዛሉ፡፡ ቢ6 የብግነት፣ በስብ ክምችት ሳቢያ የሚፈጠር የደም ቅዳ መበላሸት (atherosclerosis) እና የደም ግፊት በሽታ ተጋላጭነትን የሚቀንስ በወይን ውስጥ የሚገኝ ንጥረ-ነገር ነው፡፡
አመጋገብ፡- አዲስ የተቀጠፈ ወይን ከሌሎች ምርቶች (ለምሳሌ፣ የታሸገ) የበለጠ ነው፡፡ ወይን ቢቀዘቅዝም እንኳን በውስጡ ያሉትን አልሚ ምግቦች አያጣም፡፡ በውስጡ ያለውን ፍሬ ጭምር መብላቱ ጥሩ ነው፣ ፍሬዎቹ ለጤና ተስማሚ በሆኑ አልሚ ምግቦች የተሞሉ ናቸው፡፡ µ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

Food Safety: Keep Your Family Healthy This Summer

Next Story

Depression: What you need to know – By Eyob B Kassa

Latest from Blog

Assad Flees 1

Post-Assad Syria: Navigating Hope and Uncertainty

Dahilon Yassin The Syrian uprising against Bashar al-Assad’s regime which escalated into a civil war was violently crushed by the Syrian government in 2011. 13 years later, a surprise rebel offensive reached
Go toTop