በፓርላማው ብቸኛው ተቃዋሚ ግርማ ሰይፉ በሚኒሶታ ሕዝባዊ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው
(ዘ-ሐበሻ) የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የሚኒሶታ የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫ “በኢትዮጵያ ፓርላማ ብቸኛው ተቃዋሚ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ወደ ሚኒሶታ በመምጣት ቅዳሜ ኤፕሪል 27፣ 2013 ዓ.ም ሕዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርጉ” ገለጸ።
የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴው ለዘ-ሐበሻ እንደገለጸው “በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ያለውን አጠቃላይ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳይ ችግሮችን አስመልክቶ በውጭ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠትና በሃገራችን ጉዳይም ከኛ ጋር ለመወያየት፤ እንዲሁም የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን መልሶ ህይወት ለመስጠት የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀ መንበርና በፓርላማው ብቸኛው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አንደበት የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ወደ ከተማችን ስለሚመጡ የሚኒሶታ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያን ወዳጆች በነቂስ በመውጣት ድጋፋቸውን እንዲሰጡን እንጠይቃለን” ብሏል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት የአማርኛ ተናጋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከሚኖሩበት ቦታ ተፈናቅለው በችግር ላይ እንዲወድቁ መደረጉ ብዙዎችን ባስቆጣበት ወቅት በሚደረገው በዚህ የሚኒሶታ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ሕዝቡ በመገኘት አቶ ግርማ የአማርኛ ተናጋሪዎችን ድምጽ በፓርላማው እንዲያሰሙ እንዲጠይቅና እንዲያሳስብ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለዘ-ሐበሻ ተናግረዋል። “የኢትዮጵያ መንግስት የአማሮቹን መፈናቀል፣ በጋምቤላ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ፣ የአፋር ክልል ውስጥ የገባውን ረሃብ፣ በኦሮሚያ ክልል ያሉ እስካሁን ያልተፈቱና እየቀጠሉ ያሉ ችግሮችን፣ በሚዲያዎቹ ጭምር ባልዘገበበትና ምንም ምላሽ ባልሰጠበት ሁኔታ አቶ ግርማ ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱ እዚህ ያለውን ድምጽ ፓርላማ ላይ ገብተው እንዲያሰሙ ለመጠይቅ ይህ አጋጣሚ መልካም ነው” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ “በሚኒሶታ የምንገኝ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ሰብሰባ አጋጣሚ እየተፈናቀሉና እየተቸገሩ ላሉት ወገኖች ድጋፋችንን የምንሰጥበትን መንገድ እናመቻቻለን” ብለዋል።
አቶ ግርማ ሰይፉ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወሩ ከኢትዮጵያውያን ጋር እየተወያዩ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከሚመለሱበት 2 ቀናት አስቀድሞ ይህን ስብሰባ በሚኒሶታ እንደሚያደርጉ ታውቋል። አቶ ግርማ ኤፕሪል 27 የሚያደርጉት ሕዝባዊ ስብሰባ በሚኒሶታ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ትላልቅ ወተር ፓርኮች መካከል አንዱ በሆነው Water Park of America (Radisson Hotel by Mall of America – Bloomington) ሲሆን አድራሻውም፡ 1700 American Blvd E Bloomington, MN 55425 እንደሆነ የሚኒሶታ የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ሰጪ ገልጿል። ለበለጠ መረጃም 612-986-0557 መደወል ይቻላል።
አቶ ግርማ ሰይፉ በሚኒሶታ የሚያደርጉት ስብሰባ ፍላየር ደርሶናል፡ የሚከተለው ነው።