Dark
Light
Today: December 23, 2024

አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ – ይወገዱ!

December 19, 2012

(ethiopianreporter) ሥልጣን ተሰጥቶት የተመደበ ሹምና ኃላፊነት የተቀበለ ሠራተኛ ትልቁ ተልዕኮአቸው ሕዝብንና አገርን ማገልገል ነው፡፡

የሚከፈላቸው ደመወዝ፣ የሚያንቀሳቅሱት በጀት፣ የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ከአገርና ከሕዝብ የመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተሿሚዎች የሕዝብ በጀት ተመድቦላቸው፣ የሕዝብ አደራ ተሰጥቶዋቸው ሕዝብን እንዲያገለግሉ ነው የተመደቡት፡፡
ይህንን አምነውና ተቀብለው የሚሠሩ ሹሞችና ሠራተኞች እንዳሉ አንክድም፡፡ በመልካም ግብራቸው የሚታወቁ የሕዝብ ወገኖች አሉ፡፡ ነገር ግን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመርሳትና በመዘንጋት ሕዝብን ከማገልገልና አገርን ከመጥቀም ይልቅ ሕዝብንና አገርን የሚጎዱ አሉ፡፡ እነዚህ ይወገዱ እንላለን፡፡
አገርንና ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ የግል ጥቅማ ጥቅማቸውን እያሳደዱ የሚውሉ ሹሞች አሉ፡፡ መፈክራቸውንና ምኞታቸውን መኪና መግዛትና ቪላ መገንባት ብቻ በማድረግ አገርንና ሕዝብን ረስተዋል፡፡ የአገሪቱን ሕገ መንግሥትና ሕጎች የሚጥሱ እየበዙ ነው፡፡
ማመልከቻ፣ አቤቱታና ቅሬታ የማያነቡ፣ የማይወስኑና የማያስወስኑ እንዲሁም ሕግን የሚጥሱ እየተበራከቱ ናቸው፡፡ ከዚህ አልፈውም ቢሮ መግባት ያቆሙም አሉ፡፡
ኢንቨስተሮች ከውጭ መጥተው የሚያስተናግዳቸውና የሚወስንላቸው እያጡ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጥያቄያቸውን መመለስና ችግራቸውን መፍታት ያለበት ቢሮ ሲሄዱ የሚያስተናግዳቸው እያጡ ናቸው፡፡
በርካታ መሥርያ ቤቶች ‹‹ወደ ፊት ሂድ›› የሚለውን መመርያ ከረሱት ሰነባብተዋል፡፡ ‹‹ከባለሀብት ጋር ሂድ›› እያሉ ‹‹ወደ ኋላ ሂድ›› የሚለውን ተግባራዊ እያደረጉ ናቸው፡፡ ሥራ ቆሟል የሚያሰኝ ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡ ነገሮች ሲቆሙና ሲቀዘቅዙ እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ ይህም በሕዝብ ወይም በባለጉዳዮች የተፈጠረ ችግር ሳይሆን በኃላፊዎች፣ በሹሞችና በሠራተኞች ሆን ተብሎ እየተፈጠረ ያለ ችግር ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም ተሰምቶ፣ ተወርቶ ወይም ታይቶ የማይታወቅ ችግር በባንኮች አካባቢ ሰሞኑን ተስተውሏል፡፡ ኔትወርክ ስለማይሠራ፣ ገንዘብ ስለሌለን የባንክ ደንበኞችን አናስተናግድም እያሉ ሲያመላልሱ እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ ‹‹24 ሰዓት ክፍት ነን›› ማለት የሚገባው ባንክ አራት ቀን ሙሉ ማስተናገድ አልችልም ሲል ታይቷል፤ ተሰምቷል፡፡
ምን እየሆነ ነው? በጣም የሚያሳስበውና የሚያሳዝነው ደግሞ ተጠያቂነት ባለመኖሩ የሚጠይቅም የሚጠየቅም የለም፡፡ የሚቆጣጠር የለም፤ ችግር የሚፈታ የለም፡፡ መፍትሔው ገጠመኝ ሆኗል፡፡ ሕዝብን ማስተናገድ መርህ መሆኑ ቀርቶ ሎተሪ እየሆነ ነው፡፡ ያውም የሚገርም ሎተሪ፡፡ ትኬት ያልቆረጡ ሰዎች ሎተሪ ደርሷችኋል ተብለው የሚስተናገዱበት ሎተሪ፡፡ የሎተሪ ትኬት ሳይቆረጥ ‹‹ቼክ›› ስለሚቆረጥ፡፡
አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ አገርና ሕዝብ በእጅጉ እየተጎዱ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት  እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ሥራ ላይ መዋል የሚገባው ኢንቨስትመንት በአንዳንዱ ክልል ውስጥ ወደ 28 በመቶ አሽቆልቁሎ ይታያል፡፡ ኢንቨስትመንት ተፈቅዷል፣ ይኖራል፣ ይቀጥላል ብለው ከባንክ የተበደሩ፣ ማሽን የገዙ፣ ፋብሪካ የገነቡ ሥራ ተቋርጦባቸው ዕዳ በዕዳ ሆነው ሲቸገሩና ሲጠበቡ እየተስተዋለ ነው፡፡ አቤት ቢሉም የሚሳደብና የሚገላምጥ እንጂ ችግር የሚፈታና መፍትሔ የሚሰጥ እያጡ ናቸው፡፡
ጉዳቱ ግን የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥትም እየተጣሰ ነው፡፡ ሕዝብ በሕገ መንግሥት፣ በሕጎችና በመመርያዎች ላይም እምነት እያጣ ነው፡፡ ሥራ ላይ ካልዋለ ምን ዋጋ አለው እያለ ነው፡፡
ነገሮች እየተሻሻሉና እየተቀላጠፉ ከመሄድ ይልቅ የንግድ ፈቃድ ለማሳደስ መንከራተት በዝቷል፡፡ ፈቃድ ለመመለስ ጣጣ ሆኗል፡፡ የባንክ ብድር ለማግኘት መከራ ነው፡፡ ኤልሲ ለመክፈት ሕልምና ቅዠት ነው፡፡ ውሳኔና ፍትሕ ማግኘት ገጠመኝ ሆኗል፡፡
መሥርያ ቤቶች በሙስና ተጨማልቀዋል፡፡ የፍትሕ ተቋማት የሕግ አንቀጾችን ከመከተል ይልቅ ‹‹ደንበኞቻችን ንጉሦቻችን ናቸው›› የሚሉ መስለዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ይህንን ለማጋለጥ ሥራቸውን እየሠሩ አይደለም፡፡ ሥርዓት ጠፋ፤ ሥርዓት ታጣ፡፡
በተለይ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያለው ትልቁ ችግር የት አቤት እንደሚባል አለመታወቁ ነው፡፡ ወይ ኃላፊው የለም፡፡ ወይ ደግሞ አይወሰንም፡፡ ቅሬታ ማቅረብ ዕለታዊ የሕዝብ ሥራ ሆኗል፡፡ ቅሬታ ሰሚና ፈቺ ግን ጠፍቷል፡፡ ተስፋ በመቁረጥም ሰው አቤት ማለቱን አቁሟል፡፡
መንግሥት ግን እንዳይሳሳት፡፡ አቤት ባይ መምጣት ያቆመው አቤቱታ ስለጠፋ ሳይሆን፣ ሰሚ የለም ብሎ ተስፋ ስለቆረጠ ነው፡፡ ተስፋ የቆረጠ አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ ወዳልተፈለገ የአቤቱታ አፈታት ዘዴ ሊሄድ እንደሚችል መገመት ብልህነት ነው፡፡
ኢሕአዴግም እንደ ገዢ ፓርቲ መንግሥትም እንደ መንግሥት ብዙ ሥራ አላቸው፡፡ መፈታት ያለባቸው አስቸኳይ ሥራዎች አሉ፡፡ ቅድሚያውን ግን ሕዝብን ለማዳመጥና የሕዝብን ችግር ለመፍታት ያድርጉ፡፡
ሕዝብ እየተጎዳ ነው፡፡ አገር እየተጎዳ ነው፡፡

አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ – ይወገዱ!

Source ethiopianreporter

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

Ethiopia postponed appeal of Eskinder Nega and opposition leader Andualem Arage

Next Story

Ginbot7 Popular Force (GPF) Formation

Latest from Blog

A demon by the Bank of the Blue Nile River

By Aschalew kebede Abebe The Triangular Entanglement It had been more than a century since the foundation of the conspiracy theory had lain down. It had begun when Theodore Herzl proposed to
Go toTop