የዘሐበሻ የዕለቱ ዜና እና የኢትዮጵዊያን አመለካከት

“ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የምርጫ ቦርድን ስራ በትእግስት መጠባበቅ ይገባል” አቶ ቃሬ ጫዌቻ(የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ)

4 mins read
3

የክልልነት ጥያቄው በህገ-መንግስቱ መሰረት ምላሽ እንዲያገኝ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስራ በመጀመሩ መላው የሲዳማ ብሔር ተወላጆች በትዕግስት እንዲጠባበቁ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ ቃሬ ጫዊቻ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ዙሪያ ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ እንዲቻል ቅድመ-ዝግጅቱን ጀምሯል።

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ህዝበ ውሳኔውን ለማድረግ እንዲያስችል በደቡብ ክልልና በሲዳማ ዞን መከናወን ያለባቸውን ተግባራት በመለየት ማሳወቁንና እስከ ሐምሌ 19 ድረስ ዝርዝሩን በጽሁፍ ማቅረብ እንዲቻል የጊዜ ገደብ መስጠቱን አስታውቀዋል።

የሲዳማ ዞን አስተዳደር ከክልሉ መንግስትና ከደኢህዴን ጋር በመሆን በጥያቄው ዙሪያ በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙና ምርጫ ቦርድ በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንደሚደረግ በመግለጹ መላው የሲዳማ ተወላጆችና ወጣቶች ጉዳዩን በትዕግስት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

ቦርዱ በህዝበ ውሳኔ ማደራጀት ዙሪያ ከሲዳማ ዞንና ከክልሉ መንግስት ጋር በተለያዩ ጊዜያት መወያየቱን ያስታወሱት አቶ ቃሬ ህዝበ ውሳኔውን አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ አደራጅቶ ለጥያቄው አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል