የዘሐበሻ የዕለቱ ዜና እና የኢትዮጵዊያን አመለካከት

ተስፋዬ ቤልጂጌ – አሁንገና ዓለማየሁ

35 mins read

ቤልጂግ ማለት የድሮ ጠመንጃ ስም ነው። ተስፋውን በሕዝቡ ወይንም በአምላኩ ላይ ያላደረገ መሪ ተስፋውን በመሣሪያ ላይ ያደርጋል። “አፈ ሙዝ ነው ተስፋዬ” ይላል ማለት ነው። ወያኔ ተስፋዬ ቤልጂጌ ነበረች። ብልጽግናም ተስፋዬ ቤልጂጌ ነው። ተስፋው በመሣሪያ ላይ ነው። ጠመንጃን ተስፋ ያደርጋል። ፈሪሃ እግዚአብሄር በራቀው ብቻ ሳይሆን ሲዖላዊ በሆነ የጭፍጨፋና የሽብር፣ የቅጥፈትና፣ የድራማ የአስተዳደር ዘይቤ ሃገሩን እየመራ ነው። በዚህ የጥፋት ሥራው መተማመኛና ዋና መመኪያ ያደረገው ቤልጂጉን (ታንኩን)፣ መሣሪያውን ነው።
እርግጥ ከወገን ይልቅ በመሳሪያ ላይ መተማመን አዲስ አይደለም። የሚከተለው ግጥም ይህንን ዝንባሌ ያመለክታል።

አምጡት ምንሽሬን ቢለየኝ አልወድም
አምጡልኝ ቤልጂጌን ቢለየኝ አልወድም
ደም ከደረቀ ነው የሚደርሰው ወንድም።

ይህ ግጥም ወገን ቢኖርህም ወገንህ ከጥቃት ሊከላከልልህ የሚደርሰው ከሞትክ በኋላ ነው። ይልቅ ራስህን የምትከላከልበትን መሣሪያ በቅርብህ ማድረጉ ነው የሚበጀው። የሚል መልእክት ነው ያለው።

ይሁን እንጂ ይህ ራስን ስለመከላከል የተደረሰ ግጥም እንጂ ስለ ማጥቃት፣ ስለማሳደድ፣ ስለ ሀገር አስተዳደር የተጻፈ መመሪያ አይደለም።
ሱዳን መጣ፣ ግብጽ መጣ ይሉናል። ከሱዳን በላይ ሱዳን፣ ከግብጽ በላይ ግብጽ፣ ከፋሺስት ጣልያን በላይ ፋሺስት ሆነው ቤት ዘግተው እያነደዱን፣ ሙሉ ቤተሰብ እየፈጁ፣ በመቶ ሺህ አያፈናቀሉ፣ እንዴት ወገን ይባላሉ? ጣልያንስ ሌላ ምን አደረገ? ሊቁ ዓለማየሁ ሞገስ ፋሺስት ጣልያን ተወግዶ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን ባለውለታ አርበኛው በላይ ዘለቀን የሰቀሉት ጊዜ እንዲህ ብለው ገጥመው ነበር።

ቁርጥምጥም አድርጎ ሰውን ከበላው
ነጭ ጅብ ጥቁር ጅብ ምንድን አሰኘው?

ወያኔ ሆነ ኦህዴድ/ ብልጽግና ሰው በላ ከሆነ ሰው በላ ነው። ታላቋ ትግራይ፣ ታላቋ ኦሮሚያ የሚሉ ቅዠቶች፣ እንደ ታላቋ ሶማልያ ቅዠት ካልጋ ሲሉት አመድ የሚያደርጉ እብደቶች ናቸው።

Mancho Kam
JatSnupdmsaoerurnsnoy fr3,a 20fu2cee0dScSi ·
#ጥንቃቄ
“ጅብ የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” አሉ። ተስፋዬ በልጂጌ ማነው?
የደቡብ ክልል ባለስልጣናት እያሉ፣ ከምባታን በመከፋፈልና በማጋጨት ጥቅሙን እንዲያጣ ያለመታከት ሲሰሩ የነበሩ ሰው ማን እንደሚባሉ ያውቃሉ?
ተስፋዬ ቤልጂጌ ይባላሉ። ጎፋ የሚባል አዲስ ዞን ፈጥረው አሁን ደግሞ በአንድ አመት የራሱ ክልል እንዲኖረው ካረጋገጡ በኋላ፣ አሁንም በከምባታ ላይ ደባ ለመስራት ዛሬ ዱራሜ ገብተዋል። የከምባታን ምሁራንና ህዝብ ተስፋዬ በልጂጌ የፖለቲካ ሀሁ ለማስተማርና ለማታለል፣ የእስካሁኑ የመከፋፈል ሴራው ሳያንስ እዛ መገኘቱ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ለከምባታ ስድብ ነው።
የእስከዛሬ ደባው ከዛው አካባቢ ለሆዳቸው የሚሞቱ ካድሬዎችን አዘጋጅቶ ሀሳብ መከፋፈልና እርስበርስ ማጋጨት መሆኑን መርሳት አይገባም። ለዚህ አዘጋጅቶ ከአዲስአበባና ከሀዋሳ ያመጣቸው ሆዳሞች መኖራቸው ተረጋግጧልና ጥንቃቄ ይደረግ።
የከምባታ ጠምባሮ ፖለቲከኞች በዚህ ሰው ተደልለው ሆሳእና ለመለጠፍ እንዲስማሙና የህዝቡን ፍላጎት እንዲያፍኑ መታሰቡ በራሱ በጣም አሳፋሪ ነው። ይህ ሰው ነገ በቀጥታ ሊነገረውና “በቃህ!”ሊባል ይገባል።
“አገኖሲ መኒ ከኒች አባ ኩሌኖባ። … ከን ኘንቺ አገኖሲጋ ኩሉ ሀሲሰኖ። ከምባቱ ገጋስ ገሸኖ ወቃ ሀሱን።”
ቸር እንሁን።
(ታህሳስ 24/2012 ዓ•ም)

ተስፋዬ ቤልጂጌ የተባለ የሕወሃት ዘመን ወንጀለኛ፣ በደቡብ ቤተክርስትያንን ሲያዋርድ፣ የቤተክርስትያን ንብረት ሲዘርፍ፣ የተዋሕዶ ፣ምእመናንን ሲያሳድድ የነበረ የኢህአዴግ/የብልጽግና ባለሥልጣን፣ የመተከልን ጭፍጨፋ ከአሻድሊ ጋር ሆኖ መፍትሔ እንዲሰጥ በዶ/ር ዐቢይ ተሹሟል። ዶ/ር ዐቢይ በጎጃም ተወላጆች ቁስል ላይ የጋለ ብረት መሰካትን ለምን እንደመረጡ እሳቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት። ዛሬም እለት እለት በመተከል መንደሮችና ጫካዎች ኢትዮጵያውያን ይጨፈጨፋሉ። የንጹሐኑ፣ በግሬደር የተቀብሩት፣ ከእልቂት ተርፈው በዱር በገደሉ የተሰደዱት፣ በየከተማው ታዛ የወደቁት የደሃ ገበሬ ቤተሰቦች ደም በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እጅ ነው።* ትህነግን የተፋረደ የንጹሐን ደም እሳቸውንም እንደሚፋረዳቸው መጽሐፍ ቅዱስና የኢትዮጵያ ታሪክ ያስተምሩናል። መንገዳቸውን በጊዜ ቢያርሙ ለሳቸውም ለኢትዮጵያም ይበጃል።
የሚከተለውም ሁለት ስንኝ የአማርኛ ኅብር ቅኔ ይህንን ያስገነዝበናል።

ጣና ማዶ ሆኖ ምን ያወራል ጉና
ይዘገያል እንጂ አይቀርም ደመና

(እንዴት ይፈታል? ሰሙ ፤ ከጣና ማዶ በሩቁ የሚታየው የጉና ተራራ፣ እጅግ ደጋማ በመሆኑ ደመና አይለየውም። አሁን ጉምና ደመና ባይታይበትም እንኳን በኋላ ግን አይቀርም፣ ይሸፍነዋል። ወርቁ፤ ደም ከንቱ ወይም መና ሆኖ አይቀርም። የፍርድ ቀን ይመጣል ማለት ነው)
እውነት ለመናገር የሕወሃትና የኦነግ ከባእዳን የተቀዳ የአማራና የተዋሕዶ ጥላቻና ፍራቻ የዐቢይ አህመድን ሥነ ልቡና በበሽታነት ደረጃ የተቆጣጠረው ይመስላልና ከዚህ ጽኑ ደዌ እንዲፈወሱ ልንጸልይ ይገባናል። ካልተፈወሱ፣ በሳቸው የሥልጣን ዘመን ይህንን ሕዝብ ገናም የከፋ መከራ ይጠብቀዋልና። በተከታታዮቹ የመተከል እልቂቶች ሳቢያ በጉብኝት ስም ያቀነባበሩት አስጸያፊና ነውረኛ ድራማ ባስከተለው ተጨማሪ አስከፊ እልቂት ማግስት አሻድሊና ተስፋዬ ቤልጂጌን ችግር ፈቺ አድርጎ ማስቀመጥ ከጤነኛ ሕሊና ሊፈልቅ አይችልም።
ጋዜጦች የባለሥልጣኑን ስም ተስፋዬ ቤልጂጌ፣ ቤጂጋ፣ ቤጂጌ በሚል የተለያየ ስም ይጽፋሉ። እዚህ ላይ ለሥነ ጽሑፉ እንዲመቸን የመጀመሪያውን ተጠቅመናል። የስምን ጉዳይ ካነሳን አንድ ስም እንጨምር።

አድጎ አምሳያ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ባለሥልጣን የነበረ፣ በፌደራል መንግሥትም እስከ ሚንስትር ዴታ የተሾመ የጉሙዝ ተወላጅ ሰው ስም ነው።
ከዘመኑ ጋር አገናዝበን ስንተረጉመው ኦህዴድ ተወልዶና አድጎ የሕወሃት አምሳያ ሆነ የሚል ምሳሌያዊ ፍቺ ይሰጠናል። ሕወሃት የሚሠራውን ሁሉ ያውም አስበልጦ፣ የበለጠ ቀፋፊና ዘራፊ፣ ተስገብጋቢና ጠቅላይ ሆኖ እየሠራ ነውና ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እያስባለ ነው። አምሳያነቱ ፍጹም ስለሆነ አድጎ ሕወሃትን ተካው ለማለት ኦህዴድን የሚገልጽ ግሩም ስም ይወጣዋል። አድጎ አምሳያ።
ይህ አድጎ የተባለ የጉሙዝ ተወላጅ አማራ የሆኑ ቤተሰቦች ያሳደጉት ተመልሶ ያሳደጉትን አጥፊ መሆኑ፣ የኦህዴድን በሕወሃት ማደጎ የማደግና መልሶም ሕወሃትን ማጥፋትም የሚያሳይ ምሳሌነት አለው።

ሶስተኛም አንዳንድ ጋዜጦች ላይ ‘ሃድጉ አምሳያ’ ብለው የትግሪኛ ስም የሚመስል ይጠቀማሉ። በዚህ በትግሪኛውም ስም ብናየው ሃድጉ የሚለው ስም በኤርትራና በትግራይ ለልጅ የሚሰጠው ከወላጅ አንደኛቸው ሲሞቱ ‘ተካልኝ’ ወይም ‘ተወልኝ’ ለማለት ስልሆነ ሕወሃት ሲሞት ኦህዴድን ተካልን በሚል ልናራቅቀው እንችላለን። ‘ሃድጉ አምሳያ’ ካልን አምሳያ የሆነ እሱን ራሱን ቁርጥ የሚመስል ተክቶልን ሄደ ማለት ይሆናልና ለሕወሃትና ለወራሹ ለኦህዴድ የሚገባ ገለጻ ይሆናል።

ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ በኋላ አድጎ አምሳያ የተባሉት ጨፍጫፊ የጉሙዝ ተወላጅ በቁጥጥር ሥር ውለዋል የሚል ዜና ተሰምቷል። መልካም ጅማሬ ነው። የሕወሃት አምሳያ የሆኑት አስተሳሰብችና ሥርዓቶች ከሀገራችን ተወግደው የሰላም አየር የምንተነፍስ ያድርገን።
ሕወሃትን – ነፍስ ይማር
ብልጽግናን – ከጎሳ ደዌ ፣ ከአምሳያነት በሽታ ይፈውስ
እንላለን።

 

አሁንገና ዓለማየሁ
________
*በመተከሉ የግፍ ሥራ ብልጽግና እና ዶ/ር ዐቢይ በሚሳሱለት እና ጁንታዬ እያሉ በሚያቆላምጡት ሕወሃት ሊያሳብቧቸው የማይችሏቸው የገዛ የግል ንብረታቸው የሆኑ ክፋቶች ማሳያዎች እነሆ (የሕወሃት ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው)

• ሽመልስ አብዲሳ የመተከልን ዲሞግራፊ በኦሮሞ ስለመቆጣጠራቸውና ስለቀጣይም እቅዶች የተናገረው ንግግር
• ዶ/ር ግርማ አመንቴ (የጎጃም ኦሮሞ) በኦሮሚያ ከፍተኛ ባልሥልጣንነት በመተከል የሚያሳልጠው የኦነጉማ ሥራ
• አሻድሊ ሃሳንን ጨምሮ የመተከል የሕወሃት ዘመን ጭፍጨፋ አሳላጮች በብልጽግና ዘመን ከበፊቱ እጅግ የከፋ ጭፍጨፋና ማፈናቀልን መርተው እየተሾሙና እየተሽሞነሙኑ መሆናቸው።
• ዶ/ር ዐቢይ በመተከል ጉብኝንት ማንንም ሕጻን የማይሸውድ ቀሺም ግን እጅግ አደገኛ የጂኖሳይድ ቅስቀሳ ድራማ መመድረካቸው። ከጨፍጫፊው ጎን ተቀምጠው፣ ጨፍጫፊው አስቀድሞ የተዘጋጀበትን የዘር ፍጅት ቀስቃሽ መልእክትና አሳፋሪ ቅንብር በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ ማድረጋቸው፣ በስብሰባው እውነተኛ የተጠቂ ወገን ያልተሳተፈ መሆኑ አስተዛዛቢና አሳፋሪ ከሀገር መሪ የማይጠበቅ ተግባር ነው። በስብሰባውም ስለተጠቂዎች የተጠቀሙት ቋንቋ እጅግ አሳሳች ነው። ተጠቂዎች ሁሉ ከሌላ ክልል የመጡ በማስመሰል ተናግረዋል። አማራ፣ አገውና ሺናሻ የመተከል ጎጃም ባለርስቶች ናቸው።
• የዶ/ር ዐቢይን ጉብኝት ተከትሎ አጅግ አስከፊ ጭፍጨፋ ሲካሄድ እሳቸው ያስተላለፉት አቃላይና ፌዘኛ መልእክት። እንደ መሪ ሀገራዊ ሃዘን እንዲታወጅ ማድረግ፣ ተጓዳኝም የእርዳታ ጥሪ ማስተላለፍ ሲገባቸው።
• የችግሩ ሰለባዎች በግሬደር ባንድ ጉድጓድ እንዲቀበሩ መደረጉ። ይህንን በሕወሃት ማሳበብ ይቻላል?
• ችግሩን ለመፍታት ብለው የመደቧቸው በደቡብ ዘረፋና ጭፍጨፋ ሲመሩ የነበሩትን ተስፋዬ ቤልጂጌ እና የቤንሻንጉሉን አንጋፋ አስጨፍጫፊ አሻድሊ ሃሰን ዓይነቶቹን መሆኑ
• በመተከልም ሆነ በወለጋ የሚደረገው ጭፍጨፋ ሲካሄድ ብልጽግና በሚቆጣጠራቸው ሚድያዎች እነዚህን ዜናዎች የሚደፍቅ የተቀነባበረ የማስቀየሻ የሚድያ ዘመቻ ማካሄዱ። ይሄም በሐሰት ተያዙ፣ ተደመሰሱ የሚላቸውን የሸኔ ታጋዮች ዜና ይጨምራል።
• ተላከ ወይም ተመደበ የሚባለው መከላከያ፣ ኮማንድ ፖስት ወዘተ ተሻለ ሲባል ችግር ከደረሰ በኋላ የሚደርስና የቀብር አስፈጻሚ ሥራ እንዲሠራ የተደረገ መሆኑ
• ችግሩ እንዳይፈታ፣ ሕዝቡ ራሱን የሚከላከልበትን መሣሪያ እንዳይታጠቅም ሆነ የታጠቀ ልዩ ኃይል ከአማራ ክልል ገብቶ እንዳያረጋጋ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.