የዘሐበሻ የዕለቱ ዜና እና የኢትዮጵዊያን አመለካከት

የኀጢአት እና የፅድቅ ፍሬዎች … መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

49 mins read

ምዕራፍ፡11

1፤ አባይ፡ ሚዛን፡ በእግዚአብሔር፡ ፊት፡ አስጸያፊ፡ ነ ው፤  እውነተኛ፡ሚ ዛን፡ ግን፡ ደስ፡ ያሠኘዋል።

2፤ ትዕቢት፡ ከመጣች፡ ውርደት፡ ትመጣለች፤ በትሑታን፡  ዘንድ፡  ግን፡ ጥበብ፡ ትገኛለች።

3፤ ቅኖች፡ ቅንነታቸው፡ ትመራቸዋለች፤  ወስላታዎችን፡ግን፡  ጠማማነታቸው፡  ታጠፋቸዋለች።

4፤በቍጣ፡ቀን፡ሀብት፡አትረባም፤ጽድቅ፡ግን፡ከሞት፡ ታድናለች።

5፤የፍጹም፡ሰው፡ጽድቁ፡መንገዱን፡ያቀናለታል፤ኃጥእ፡ ግን፡በኀጢአቱ፡ይ ወድቃል።

6፤ቅኖችን፡ጽድቃቸው፡ይታደጋቸዋል፤ወስላታዎች፡ግን፡ በምኞታቸው፡ ይጠመዳሉ።

7፤ኃጥእ፡በሞተ፡ጊዜ፡ተስፋው፡ይቈረጣል፥የኀያል፡አለኝታም፡ይጠፋል።

8፤ጻድቅ፡ከጭንቀት፡ይድናል፥ኃጥእም፡በርሱ፡ፋንታ፡ያምጣል።

9፤ዝንጉ፡ሰው፡በአፉ፡ባልንጀራውን፡ያጠፋል፤ጻድቃን፡ግን፡ በዕውቀት፡ ይድናሉ።

10፤በጻድቃን፡ልማት፡ከተማ፡ደስ፡ይላታል፥በኃጥኣንም፡ ጥፋት፡ እልል፡ ትላለች

(መፀሐፈ ምሳሌ ፣ምዕራፍ 11 ቁ 10 )

14፤…እያንዳንዱ፡በራሱ፡ምኞት፡ሲሳብና፡ሲታለል፡ይፈተናል።

15፤ከዚህ፡በዃላ፡ምኞት፡ፀንሳ፡ ኀጢአትን፡ትወልዳለች፤ኀጢ አትም፡ ካደገች፡ በዃላ፡ ሞትን፡ ትወልዳለች

(ሦሥተኛ የያዕቆብ መልክት 1፤14_15 )

 መግቢያ

ዛሬ  ብዕሬን ያነሳሁት በሁለት አሥተማሪ ሃሳቦች ላይ ለመፃፍ  ነው።አንደኛው ሃሳብ የፈጣሪ ሃሳብን የሚያሥታውሥ ነው።ፈጣሪ የፈጠረውን ሰው ፣በቅንነት ፣በትህትና ፣በእውነት፣ በተሥፋ፣በእምነትና በፍቅር በምድር እንዲኖር ይፈልጋል።ሰውን ፈጣሪው የፈጠረው እርሱን እየፈራ እያከበረ ከላይ የጠቀሥኳቸውን እየተገበረና እርሱን ፈርቶ ከሐጢያት ተጠብቆ እንዲኖር ነው።

እናም አንደኛው ሃሳብ፣ ሰው ፈጣሪን የሚፈራ ከሆነ ደግሞ ትዕቢተኛ ና አምሳያውን የሚንቅ ፣የሚበደል፣የሚያሥጨንቅ፣የሚያሰቃይ፣የሚገድል፣የሚያፈናቅል፣ወዘተ።አይሆንም።በማለት ሰው ፍጡር እንደሆነ እንዲገነዘብና ትህትና እና ቅንነት እንዳይለየው ፣ ከላይ ከጠቀስኩት  የመፀመፍ ቅዱሱ ጠቢብ ሰለሞን ምሳሌ  አንፃር ፣ ሰው ህይወቱን ይቃኝ ዘንድ ማሳሰብ ነው።

በነገራችን ላይ ሥለትዕቢት ሲነሳ “ እነ ሥብሐት ነጋ “ ዋንኛ ምሳሌ ይሆናሉ።ሰዎቹ ዝቅ፣ዝቅ፣ማለትን፣ትህትናን ሳይሆን ትዕቢትን የሙጥኝ በማለታቸው የትዕቢት ድርጊታቸው መጨረሻ ለሌሎች ትዕቢተኞች አሥተማሪ ክሥተት መሆኑንን በቴሌቪዢን መሥኮት አይተናል።በሬዲዮ ሰምተናል።በማህበራዊ ማዲያ የወደቀ ዛፍ ምሣር እንደሚበዛበትም አስተውለናል ።

ሰዎቹ ትእቢተኛ የሆኑት ፣ባላቸው ገንዘብና ሥልጣን የተነሰ ትዕቢት ወጥሯቸው ነበር።ሥልጣኑን ቢያጡትም ገንዘቡ ነበራቸው።በዛ ገንዘብም ተጠቅመው ተመልሰው ያጡትን ሥልጣን ለማግኘት ብርቱ ፍላጎት አደረባቸው። በትዕቢት የተሞላ ህሊና ነበራቸውና !  ይህ ትዕቢትም የገሃዱን    ዓለም  እውነት እንዳያዩ ገርዷቸው ነበር።በዚህም ሰበብ  መጨረሻቸው አሥጠሊታ ሆኗል።(ጅምራቸውም አሥጠሊታ ነበር የሚሉ የታሪክ ምሁራን አሉ። )

እነ “ ኦቦይ ሥብሐት “ ፣ የተደበቁበት ሥፍራንና ፣በፊት የነበራቸውን መመፃደቅ ሥናሥብ፣  ብዙዎቻችን  ፣ከዚህሥ ሞት ይሻላቸው ነበር አሰኝቷናል። ይሁን እንጂ ፣ የወንጀለኛ አቀባበል  በእልልታና ዳኒኪራ  የታጀበ ይሆናል ብሎ የሚያስብ ጤነኛ አእምሮ የሌለው ብቻ ቢሆንም ፣የቴሌቪዢኑ ዘገባ አጭርና ግልፅ መሆን ነበረበት።

ፌደራል ፖሊሥ ተረከባቸው የሚል ርእሥ ካለው  ከመቀሌ ሲሳፈሩ እና አዲስ አበባ  ደግሞ ከአውሮፕላኑ ወርደው ፌደራል ፖሊሥ ሲረከባቸው ብቻ ማሳየቱ በቂ ነበር ብዬ አሥባለሁ። ሌላው ዘገባ  ፣ በዘጋቢ ፊልም ተቀናብሮ ቢቀርብና ለታሪክ ቢቀመጥ መልካም ነበር። ሰው ያልተገነዘበው ሰዎቹ ከገደሉ ሲወጡ በምን ዓይነት ሁኔታ ውሥጥ እንደነበሩ የመሥለኛል።ደግሞም የአገሬ ህዝብ ፈሪሃ እግዛብሔር ሥላለው ጠላቱን እንኳ ማሰቃየት አይፈልግም።ለዚህም ብዙ ዋቢዎችን ከታሪክ መዛግብት መጥቀሥ ይቻላል። …

ወደ ርዕሴ ልመለሥ። ሁለተኛው ሃሳቤ ፣ በትእቢት የሚሞላን የወደፊቱ ቴክኖሎጂ ነው ብዬ አሥባለሁ።ይህ ቴክኖሎጂ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ይባላል።ይህንን ቴክኖሎጂ በጥበብ ካልያዝነው በሥተቀር  ፣ሰውን ከተፈጥሮ ውጪ በማደረግ፣ፈሪሃ እግዛብሄር የሌለው ከንቱ ያደርገዋል። የሚል ነው።

ለዚህም ነው የፅሑፌን ርእሥ እጅግም ሥለት ይቀዳል አፎት እጅግም እውቀት ያደርሳል ከሞት። “ያልኩት።መልካም ንባብ።

 

 ከመፅሐፍ ቅዱሱ ምሳሌ ምን እንረዳለን

ይህ የመፀሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ብዙ ነገር ያሥተምረናል።ከተማርንበት።በዚህ ምሳሌ ውሥጥ አባይ ሚዛን፣ትዕቢትና ትህትና፣ወሥላታ፣ጻድቅ  ና ኃጥአ ፣ዝንጉ ፣የሚባሉ ቃላቶች በየራሳቸው እንደአንድ አርሥት ወሥደን ልንወያይባቸው እንችላለን።

አባይ ሚዛን የአጭበርባሪነት መገለጫ ነው። ሥለፍትህ መጓደል ወይም በእውነት እና ፈጣሪን በመፍራት ሰውን ያለማገልገል ምን ያህል አፀያፊ እንደሆነ የምንገነዘበው አባይ ካልሆንን ብቻ ነው።በትዕቢት ከተወጠርን ግን አባይ ነን።

ትዕቢተኛ ሰው አባይ ነው።ዘወትር ይዋሻል።ራሱን ይቆልላል።በቅጥፈተም ራሱን ወደመለአክ ደረጃ አሥጠግቶ ሳያሥበው   ወደ ውድቀቱ የሚያመራ  ዝንጉ ሰው ነው።ማሥተዋል የሌለው…

ትዕቢተኛ ሰዎች ማሥተዋል ሥለሚጎላቸው ዛሬ ና አሁን የሚያንቀባርር ወላጅ ፣ እጅግ የፈረጠመ ደርምሶ የሚጥል ጉልበት ፣ የተትረፈረፈ ሀብት፣   ውበት ና ቁንጅና ፣ወዘተ ። አለኝ ብለው፣ከፈረሃ እግዚአብሔር ርቀው፣በራሳቸው ኃይለና ፈቃድ የየቀን ኑሯቸውን በማናለብኝነት በጥጋብ ሰማይን በርግጫ እያሉ የሚኖሩ ወሥላቶች  ናቸው።

ጽድቅና ሐጥያት የሚባል ነገር ለእነዚህ ወሥላቶች ተረት፣ተረት ነው። በጎ ነገርን ለአምሳያው ሰው ማድረግ ፣በራሥ ላይ እንዲደረግ የማየፈቅዱትን ፀያፍና ዝግናኝ ድርጊት በሌሎች ላይ አለመፈፀምም የጻድቅ ተግባር መሆኑንን ፈጽሞ አያምኑም።  “ይህ ደካማነትና ልፍሥፍሥነት ነው።በዚህ አይነት እንዴት መንጋውን እንዳሻህ  ልትነዳ ትችላለህ ባዮች ናቸው።በትዕቢት ሥለተወጠሩም ሁሌም የሚሰግድላቸውን የፈልጋሉ።መሥገድ ግን ያለብህ ለአንድ ፈጣሪህ ነውና አትሰግድላቸውም።እናም በትዕቢት ሊያሰግዱህ ሲጥሩ የናቡከደናፆር እጣ ይደርስባቸዋል።   …

 

     “ሁሉ ነገር አርቴፌሻል…”

 ( የዘሪቱ ለገሰ ዘፈንን ያደምጧል )

በአሁኑ ወቅት የከተሜ ሰው ኑሮ በሐጥያት የተከበበ ነው። በአርቴፊሻል ኑሮ የተሞላ ነው። ተፈጥሯዊ አኗኗር በከተማ ውሥጥ በርቅ ሆኗል።

ከምትገዙት ዕቃ እና ልብስ ጀምሮ ተፈጥሯዊነታቸው ላይ  የሚጨመርባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉ።ሁሉም ከድርና ማግ ብቻ አይሰሩም። …

የምትመገቡት ምግብ ተፈጥሯዊ አይደለም።ሥጋው የፉሩሽካ ቱሩፋት ነው።  በዛ ላይ ከብቱ ቶሎ፣ቶሎ በልቶ በሦሥት ወር እንዲጠበድል መድሃኒት ይሰጠዋል።  እንጀራውና ዳቦው የማዳበሪያ ውጤት ነው። በርገራችሁ ላይ፣ፒሣ ወይም ቂጣችሁ ላይ ብቻ ሣይሆን ሌሎች ምግባችሁን የሚያጣፍጡ ሰው ሰራሽ ፈሳሽና ደረቅ ንጥረ ነገሮች አርቴፊሻሎች ናቸው። የከተሜ ሰውን አቅመ ቢስ ና የሥኳር ፣የጉፋን እና የቁርጥማት ህመም ተጠቂ ያደረገው የኽ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ አመጋገቡ ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው?

እውነቴን እኳ ነው፣ለምን ማቱሳላ በ969 ዓመቱ ፣ አበርሃም ደግሞ በ930  ዓመቱ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ?… ዛሬ እንኳን ዕድሜ ሊጠገብ ይቅርና ከበሽታ ና ከወረርሺኝ ተጠብቆ  መሰንበት እጅግ ከባድ ሆኗል።ሰው ይኽንን የማይቋቋመውን ወረርሺኝ ያመጣው በገዛ እጁ ነው።እንዴት ብትሉ ተፈጥሯዊነትን በማኮሰስ አርቴፊሻልነትን አግዝፎ ለማሣየት ሌት ተቀን በመጣሩ ፣የተፈጥሮን ፀጋ ና በረከት በዝንጉነቱ  ሥለአጣ ነው።

ሰው ፈጣሪ እንደገና ከድንግል ማርያም ተፈጥሮ፣ በኢየሱስ በኩል ሰው ሆኖ፣ በመጥመቁ ዮሐንሥ ተጠምቆ ፣ በምድር የሦሥት ዓመት የመምህርነት ቆይታው ሥለፍቅር፣እምነትና ተሥፋ  ቢያሥተምረውም ፣የእግዚአብሔርን ጥበብ መመሪያው ለማድረግ እሥከዛሬ ያልቻለው ተፈጥሯዊነትን አኮስሶ አርቴፊሻሉን በማግዘፉ ነው። አርቴፊሻልነትን በዕየለት ደርጊቲ እያገዘፈ ተፈጥሮን እያኮሰሰ እንደሚገኝ በየዕለት ኖሯችን እንገነዘባለን ። የአርቴፊሻል ኑሯችንንም ከተሜዎች መመሥከር አያዳግተንም።

የከተሜውን  አርቴፊሻል ህይወት   በይበልጥ የሚያሳብቀው ፣ብልጭልጭነቱ እና ታይታን መውደዱ ነው።ይህ ብቻ አይደለም የጨለማ ድግሱም በአርቴፊሻል የተሞላ ነው።ጀንበሪቱ ሥትጠልቅ ነው የከተማ እብደት በአርቴፊሻል መልኩ ብቅ የሚለው።አጓጊ ገፅታው ሀሉ ኢ ተፈጥሯዊ ነው።   ሰዉ እራሱ     ከጨለመ በኋላ አርቴፊሻሉን አሥረሽ ምቺው የሚጀምረው በአርቴፊሻል እየነሆለለ ነው። ሣይንሱ የበሽታ መተላለፊያ መንገዶችን እየጠቀሰ ከገዳዩ ኮቪድ ተጠንቀቁ ቢልም ቅሉ፣ “ኮቪድ ሆይ ኧረ የትነህ ያለኸው ?” ባዩ የትየለሌ ነው።

አመትባልን ሰበብ አድርጌ ፣አንዳንድ መዘናኛ ሁቴሎችን እንደጎበኘሁት  በአዳማ ከተማ ሰው ታሥሮ እንደተፈታ ጥጃ ይቦርቃል። በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ጭብል አልባ የሆኑ እህቶቼም የመንገዱን ጥግ ሞልተውታል። ከእንጀራ ፍለጋ አንፃር አንዳንድ ሆቴሎች ያሉ ሴቶች ከሚዝናናው ሰው እኩል ናቸው።

እናም ሞቅ ያለው ወንድ በደብዛዛው መብራት እና ብልጭ ድርግም በሚለው መብራት አማካኝነት፣ በሚያየው የተራቆተ የፊት ውበት እና  የሥብ ክምችት የሆነውን … ፣ ሽንጥና ዴሌ… እንጂ የሴቷን የውሥጥ ንፅህና ጥያቄ ውሥጥ አያሥገባም።ለነገሩ ሥለራሱ ንፅህና የሚያውቅ ሥንቱ ነው?  “ ከእናንተ ኃጥያት የሌለበት አሥቀድሞ ይውገራት። “ ኢየሱስ  ያለው ለዚህ ነው።ሊፈትኑት ዝሙት ሥትፈፅም ያገኞትን ሴት ይዘዎት መጥተው በፊቱ ሲከሷት።ያሐፈጣሪ በሥተቀር ማንም የማንንም   የቆሰለ ልብ ሊገነዘብ አይችልም። ካለ “ አንድዬ “ በሥተቀር።

በዓለማዊ አተያይ  ፣ እርግጥ ነው፣ ወሲብ ተፈጥሯዊ ነው።እያንዳንዱ ሰውም ለድርጊቱ ያለው አሥተሳሰብ ይለያል።  በዚህ ጉዳይ ላይ ማንንም መርገምና መውቀሥ አይቻልም። የሚያሳዝነው ግን  ዛሬ ወሲብ አርቴፊሻል መሆኑ  “ ወዴት እየሄድን ነው ?  “ የሚል ጥያቄን ያጭራል ። ድርጊቱ ከፈጣሪ ጋር የሚያጋጭ      ሐጥያት እንደሆነ አያከራክርም።።…

ብዙው ወንድ ከኃይማኖት አንፃር ፣ሰውን በፈጠረው እግዜር ድርጊቱ ሲመዘን ፣በጭለማም ይሁን በብርሃን ሐጥያት መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ነው ፣እያንዳንዱ ለአቅመ አዳም የደረሰ ሴትና ወንድ ሁሉ  ፣አርቴፊሻል  ድርጊቱ ሐጥያት መሆኑን ተገንዝቦ ፣ ከድርጊቱ በኋላ ፈጣሪ ይቅርታ እንዲያደርግለት በፀፀት በውሥጡ የሚያነባው ።

በበኩሌ እራሱን በአርቴፊሻል ነገር አሥታጥቆ በማሥክ አፉን ሸፍኖ ፣ በኮንደም ተጠቅሞ ወሲብ የሚፈፅም ሁሉ ፣ሌላ አማራጭ አጥተው በየጎዳናው እና በየሆቴሉ ለእለት ጉርሥና ለዓመት ልብሥ ብቻ ሣይሆን ደሃ ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ብለው ፣በዚህ በኃይማኖት ተወጋዢ ድርጊት ላይ የተሰማሩትን እንደረዳቸው እቋጥረዋለሁ። ተፈጥሯዊ ያልሆነ ድርጊቱ ተፈጥሮን ከአደጋ ለመጠበቅ ነውና ምንም ማድረግ አይቻልም።…

አንዳንዴ ሣሥበው ግን፣ ሳይንሥ እና ቴክኖሎጂ አርቴፊሻልነትን ያሥፋፉ ይመሥለኛል። ደሞም ነው። በአሁኑ ዓለም እንኳን የሰው ልጅን የከተማ አኗኗር ቀለል ያደረገው  “ አርቴፊሻል ኢንተለጀንሥ “  ኑሮ ቢያዘምንም  አንዳንድ የረቀቁ ፈጠራዎቹ ሰውን ከተፈጥሮ ፈፅሞ እየለየው ነው።

ለምሳሌ በሰውነት ወሥጥ የሚቀበርን “ ማይክሮ ቺፕሥ “እንመልከት። በአውራ ጣትህ ማሐል በሚገኝ የላይኛው ቆዳ ላይ ማይክሮ ቺፕሥ ይቀበራል። በቀላል ዘዴ።ለዚሁ በተሠራ መርፊ አማካኝነት።ከዛም አንተ በዛ ማይክሮቺፕ አማካኝነት ማንኛውንም  ሥራ መቆጣጠር ትችላለህ።በየወቅቱ ግብርህን አሥልቶ ይከፍልልሃል።የሥኳር ህመምተኛ ከሆንክ በየወቅቱ ጤንነትህን እየተከታተለ ያሣብቃል።ከአቅም በላይ ከሆነም ጠቁሞ አቡላንሥ ይጠራልሃል። የቤትህን ማንኛውንም ሥራ በዚህ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንሥ ውጤት መከወንም ትችላለህ።መብራት ማብራት፣ በር የመክፈት ና የመዝጋት፣ወዘተ። በዚህ የሣይንሥ ና የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠቅመህ በቀላሉ ታከናውናለህ።

በቤትህ ውሥጥ ያሉት የኮፒዊተር መሣሪያዎቸ እና የእጅህ ሥልክ ከእዚህ መሣሪያ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የምትፈልገውን ሥራ በቀላሉ መከወን ትችላለህ። ይሁን እንጂ የአንተ ግላዊነት በአምራቹ ካፓኒ    መዳፍ ውሥጥ መሆኑንን እወቀህ ለዚህ ማይክሮ ችፕ ሁለተናህን እንደሰጠህ ተገንዘብ።እንኳን አንተን ወደህ የገባኸውን ይቅርና  የከተሜውን ኑሮ ሣይንሥና ቴክኖሎጂ በየጓዳው ዘው ብሎ እየተቆጣጠረው ነውና የሚቀበረው ማይክሮ ቺፕሥ አይግረምህ።

በአሁኑ ወቅት ዓለምን ሣይንሥና ቴክኖሎጂ እየተቆጣጠራት መሆኑ እርግጥ ነው። በአርቴፊሻል ኢንተለጀንሥ።ማይክሮ ቺፕሥም  አዲስ ቴክኖሎጂ ነውና በቅጡ ተፈትሾ፣ለተፈጥሯዊው ሰው የሚሥማማ ካልሆነ፣እጅግ አደገኛ ነው።በዚህ አይነት ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሰውን ቁጥር ለመገደብ የሚሞክሩ ሣይንቲሥቶች ካሉም አደገኝነቱ እጅግ የከፋ ይሆናል።ምክንያቱም ዕድሜ ገዳቢና ገዳይም ሊሆኑ ይችላልና!

ለማንኛውም የቴክኖሎጂው ባለቤቶች ቆርጠው ከገፉበትና የከበርቴ አገራትን ይሁንታ ካገኙ፣  ይህ አርቴፊሻል እንቅሥቃሤ   እኤአ   2050 ዓ/ም   ከተፈጥሮ ውጪ የሚያደርጋቸው ራሳቸውን  የበለፀጉትን አገራት ነው። …

የእኔ ሥጋት ፣ ሰው ፈጣሪ ከፈጠረለት  ተፈጥሯዊ አኗኗር ውጪ ፣ማይክሮ ቺፕሥ በሰውነቱ አሥቀብሮ ህይወቱን የሚመራ   ከሆነ፣ከሰው ጋር ያለው መሥተጋብር ይጠፋልና ከአውሬ እንዳይብስ ነው።እናም  ሣይንቲሥቶቹ ለጥበባቸው ሉጋም ሊያበጁለት ይገባል ባይ  ነኝ።

“እጅግም ሥለት ይቀዳል አፎት።እጅግም እውቀት ያደርሳል ከሞት።”   እንዲሉ፣ ዛሬ ላይ ሆነን ሥለ ጥበብና እውቀት ድንበር ልንነጋገርና በኑሯችን ሁሉ፣ ጥበብን የሙጥኝ ልንላት ያሥፈልጋል።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.