የዘሐበሻ የዕለቱ ዜና እና የኢትዮጵዊያን አመለካከት

ሕገመንግሥቱ ይሻሻል! ሕገመንግሥቱ ይሻሻል! ይሻሻል! ይሻሻል! – አንድነት ይበልጣል

29 mins read
3

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ – ታህሣሥ 30 / 2013 ዓ.ም.

ችግሩ ሲገለጽ፡

የረዥም ጊዜውን ብሔር ተኮር አድልዎና መገለሉን፣ ግፍና ሰቆቃውን እናቆየው፡ ከ2 ወራት ወዲህ በትግራይ ክልል የደረሰብንንና የታዘብነውን ብቻ እንደ መነሻ እንውሰድ፤ አረመኔው ወያኔ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን በምድብ ቦታዎቻቸው፣ በሰሜን ዕዝ ልዩልዩ ጦር ሠፈሮች ውስጥ በተኙበት አሳረዳቸው፡፡ የሴት ወታደርን ጡት አስቆረጠ፣ ብልት በጩቤ አስወጋ!… ወያኔ ይህን ሁሉ ዘግናኝ የክህደት ጭፍጨፋ ያስፈጸመው የትግራይ ተወላጅ በሆኑ ከሃዲ የመከላከያ አባላት እና በትግራይ ልዩ ኃይል አባላት አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ዘረኛ የክህደት ጭፍጨፋ የተፈጸመው በዋነኛነት በጥቅምት 24 / 2013 ሌሊትና በቀጣይ ቀናት ነው፤ ዘረኝነት ጥግ ሲደርስ፣ በነፍስ ተማምነው፣ ከአንተ/ከአንቺ በፊት እኔ ተባብለው፣ በበረሐ ላይ ከአንድ ኮዳ ውኃ ተጋርተው፣ ኮሾሮ (ደረቅ ብስኩት) ተካፍለው በልተው ጥምና ረሃባቸውን የሚያስታግሱ የነፍስ ጓዶችን ያካክዳል፡፡ የብሔር ፌዴራሊዝምና ጽንፈኝነት በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ስላደረሰብን የህልውና፣ የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ የፖለቲካ፣ ሥነልቡናዊና ኃይማኖት ተኮር መዓት ዝርዝርና ሙሉውን ሥዕል ማግኘት ከባድ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በወለጋ፣ በማይካድራ፣ በቤኒሻንጉል (መተከል) ከተፈጸሙት ብሔር ተኮር የግፍ ጭፍጨፋዎች ተነስተን በጊዜ መሥመር ላይ ወደ ኋላ መጓዝ ነው፡፡ የቤኒሻንጉል/መተከልን፣ የወለጋን፣  የሻሸመኔን፣ የአርሲና የባሌን፣ የምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌን፣ የሐረርና የድሬዳዋን፣ የአዲስ አበባ ዙሪያን፣ የሐዋሳና የሲዳማን፣ የጌዴዖን፣ የኮንሶን፣ የጉራፈርዳን፣ የሶማሌን፣ የምዕራብ ሸዋን፣ የጋምቤላን ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ ሕዝባችን ላይ በተራ በተራ በተለይም በአማራ ወገኖቻችን ላይ በማተኮር የተፈጸሙ የብሔር ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች በሰፊው ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ዝርዝሩን እዚያ መመልከት ይቻላል፡፡

 

መፍትሔው፡

በዘረኝነት ምክንያት ለሚፈጸሙ የማያባሩ ጥቃቶችና የግፍ ጭፍጨፋዎች፣ ፌዴራል ፖሊስና መከላከያን ማቆምና ጥበቃ ማድረግ፣ ገዳዮችን እየለቀሙ ለፍርድ ማቅረብ፣ የተገደሉትንና የተጎዱትን እንዲሁም ቤተሰባቸውን መካስና መልሶ ማቋቋም፣ እርቅ (አንዳንዴ የውሸት) ወዘተ በጣም ጥሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ለ30 ዓመታት ያህል በሙሉ ልብም፣ በከፊል ልብና ሸፍጥ በተሞላበት ልብም ተሞክረው ዘላቂ መፍትሔ አላመጡም፡፡ ምክንያቱም ዋናውን በሽታ ከሥሩና ለዘለቄታው የሚያክሙ የጥልቅ ሕክምና ዓይነት መፍትሔዎች አልነበሩም፣ አይደሉም፤ ለአናሣ ብሔር ወገኖች ወይም የብሔራቸው ልሒቃን በሥልጣን ላይ ለሌሉ ዜጎች የብሔር ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ፣ ሲፈጸምባቸው ካሣና ማቋቋም (ያውም ያልተሟሉ) ማድረግ የበሽታውን ምልክቶች ብቻ የማከም ዓይነት ጊዜያዊና ቁንጽል የመፍትሔ እርምጃዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገን፣ ኢትዮጵያችን የሚያስፈልጋት ከበሽታው ምልክቶችም በላይ በሽታውን ራሱን ከሥር መሠረቱ ማከምና የሚያክም ነው!! ለብሔረተኛነት በሽታ ፍቱኑና ዘላቂው መፍትሔ  ለበሽታው ትክክለኛውን መድኃኒት ማግኘትና መጠቀም ነው፤ ፈዋሹ መድሃኒት ብሔርተኝነትን ሥርዓት ያደረገውን ሕገመንግሥት ትርጉም ባለው መልክ ማሻሻል ነው! ሕገመንግሥቱ ሕጋዊ ዕውቅና የሰጠው፣ ያነበረውና የሚንከባከበው ብሔረተኝነት፣ ሕዝቡን ¨እኛና አነርሱ¨ በሚል ከፋፍሎ፣ በጥርጣሬና በጥላቻ እንዲተያይና አንዱ ሌላውን እንዲያሸማቅቅና እንዲያጠቃ በሩን ከፍቶለታል፡፡ ¨የዚህ/የዚያ ክልልና የመሬቱ ባለቤት አንተ ነባሩ ሕዝብ ነህ፡፡¨ ¨ሌለው እንግዳ፣ መጤ፣ ሰፋሪና ተከራይ ነው፡፡ በሕግ ጥበቃ ሣይሆን በበጎ ፈቃድህና በመንገድህ ከሄደ ብቻ ነው በክልልህ ሊኖርና ሊንቀሳቀስ የሚችለው¨ …፡፡ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ በዚህ መልክ አስጨናቂና አደገኛ እንዲሆን ያደረገው በሕገመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት እንክብካቤም ሲደረግለት የኖረው ብሔርተኝነት ነው፡፡

ስለዚህ …

ሕገመንግሥቱ ይሻሻል! ሕገመንግሥቱ ይሻሻል! ሕገመንግሥቱ ይሻሻል! …

 

መፍትሔው በማን፣ መቼና እንዴት ይምጣ? መርሆዎቹና የትኩረት ነጥቦቹስ?

 • ብሔርተኝነትንና የብሔር ፌዴራሊዝምን ያነገሡ ጸረ አንድነት፣ ጸረ እኩልነት፣ ጸረ ዴሞክራሲ፣ ጸረ ሰውና ጸረ ዕድገት የሆኑ የሕገመንግሥት መግቢያዎች፣ ዓላማዎች፣ መርሖዎችና አንቀጾች ይሰረዙ!
 • ሕገመንግሥቱን የማሻሻል ሥራ፣ ዕውነተኛና ሁሉን አሳታፊ በሆኑ የብሔራዊ ምክክርና የመግባባት መድረኮች አማካኝነት በጋራ ስምምነት ይፈጸም፤ ብሔራዊ የምክክር መድረኮች በፍጥነት ተደራጅተው በተከታታይ ይካሄዱ!
 • በምክክር መድረኮቹ ላይ፣ ሕጋዊ መስፈርቶችን ያሟሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራትና የዜጎች አደረጃጀቶች ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ዕውነተኛ የሐገር ሽማግሌዎች፣ በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሑራንና አንጋፋ ዜጎች እና በተደጋጋሚ የብሔር ጥቃት ሰለባ የነበሩ ማኅበረሰቦች ተወካዮች ተገኝተው ሙሉ አስተዋጽዖ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠር!
 • በምክክር መድረኮቹ ላይ፡
 • በጥናት፣ በመስክ ምርመራ፣ በራስ ሕይወትና በሌሎች ተሞክሮ የተገኙና የተረጋገጡ ዕውነተኛ ጭብጦች በቦታቸው ይቀመጡ፣ በልካቸውና በትክክል ይገለጹና የጋራ መግባባት ይደረስባቸው፤
 • በብሔር ፌዴራሊዝም ምክንያት ያገኘናቸውና ያጣናቸው ሁሉን አቀፍ እሴቶች፣ የሕዝብ፣ የሐገርና የትውልድ ጥቅሞች ትክክለኛ ቆጠራ ይካሄድ! እንደ ሕዝብና እንደ ሐገር፣ ማትረፋችን ወይም መክሰራችን፣ ማደጋችን ወይም መቆርቆዛችን በሐቀኛ መረጃና ማስረጃ በግልጽ ይቅረብና ይፈተሽ፤
 • ብሔርንና የብሔር ፌዴራሊዝምን በሚመለከት ያልተረጋገጡና መሠረተ ቢስ ትርክቶች፣ አመለካከቶች፣ አቋሞች፣ ስሜቶች፣ ፍርሐቶችና ምኞቶቻችን ሁሉ እንደገና ይፈተሹ፤
 • የብሔር ፌዴራሊዝም ጥቅሞችና ጉዳቶች፣ የሠሩና ያልሠሩ አካሄዶች ወዘተ በሰከነ መንፈስ፣ በሐገራዊና ወገናዊ የኃላፊነት ስሜት በጥልቅ ይፈተሹ፤

 

የትኩረት ነጥቦች

 • አንድነትና ልዩነት ከነበራቸው/ካላቸው ግንኙነት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ታሪኮችና ትርክቶች በስፋትና በጥልቀት ይፈተሹ፤ (Diversity in Unity Vs Unity in Diversity)
 • Diversity in Unity፡ ለሺህ ዓመታት አንድ ሕዝብ ነበርን፣ ዛሬም ነን፤ በአንድነታችን ውስጥ ብዝኃነት ነበረን፣ ዛሬም አለን (Diversity in Uity)፤ አንድ ሕዝብ ነን፤ የቋንቋና የባሕል ብዝኃነታችን ውበትና ጥንካሬአችን ነው፣ ሊከበርና ተገቢ እንክብካቤ ለደረግለት ይገባል፤ መላ ሐገሪቱ የሁላችንም ነች፣ ሕዝብና ዜጋ ነባርና ሰፋሪ ተብሎ አይለይም፣ እኩል ተጠቃሚ ይሆናል፣ ድምጽና ውክልና ይኖረዋል …
 • Unity in Diversity፡ ለሺህ ዓመታት ነጻ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ሕዝቦች ነበርን፣ ¨ከ100 – 150 ወዲህ በጉልበት ቀላቀሉን፤ ከ30 ዓመት ወዲህ ደግሞ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ የብሔሮች ፌዴሬሽን ሥርዓት መሠረትን፣ በፊት ልዩ ልዩ ሕዝብና ሐገር ነበርን፤ ዛሬ አንድ ሐገር ሆንን¨! ¨በአንቀጽ 39 የተጠቀሱትን መሥፈርቶች አሟልተን መገንጠል እንችላለን¨፤ ¨በብሔር ማንነታችን ላይ የተመሠረተ ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን አለን/ይኖረናል¨፤ ¨በነባርነት የኖርንበት መሬት/ክልል የኛ ነው፤ በክልላችን ብቸኛ / ዋነኛ መብት ያለን እኛ ነን፤ በክልላችን ነዋሪ የሆኑ የሌሎች ብሔሮች አባላትን በእንግድነት እናቅፋቸዋለን፣ በብሔራችን ሥርዓትና ሕግ መሠረት እናስተናግዳቸዋለን፣ እናስተዳድራቸዋለን፣ እኛ እንወክላቸዋለን፣ ድምጽ እንሆናቸዋለን¨፤

 

መርሖዎች

 • ሁሉን ተጠቃሚ በማያደርጉ ግላዊ ወይም ቡድናዊ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና መሻቶች ላይ ሣይሆን በተረጋገጡና በማይነቃነቁ ጭብጦችና ምሰሶዎች ላይ ቆመን ለችግሮቻችን – ሕዝብን፣ ሐገርንና ትውልድን ተጠቃሚ የሚያደርግ – ሥርነቀልና ዘላቂ መፍትሔ እናምጣ፡፡
 • የእርታ – ልርታ መርሆን የተከተለ ዘላቂ መፍትሔ የምናመጣበት፣ ለሁላችንም የምናገኘው ብዙ፣ ትልቅና ዘላቂ የሚሆንበት፣ የምናጣው ግን ጥቂት፣ ትንሽና ጊዜያዊ የሚሆንበትን የመፍትሔ ሁኔታ እንፍጠር፡፡ …

 

በጥያቄዬና በምክረ ሐሳቤ የምትስማሙ ሁሉ የጎደለውን ነገር በተቻላችሁ መጠን በመሙላት የጋራ ጥያቄአችንን እናጉላው!!

ፈጣሪ ይርዳን!

 

3 Comments

 1. ለኢትዮጵያ የሚበጀው ዘላቂ መፍትሔ፤ በዝረኝነትና በማጋጨት ሕዝባችንን መከራ እያሳየ ያለውን ያሁኑን ሕገ መንግሥት አስወግዶ፤ በሌላ፤ በአዲስ፤ በዲሞክራሲ፤ በአንድነት፤ በየሕግ የበላይነት፤ በሰላም፤ በኢትዮጵያዊነት፤ ወዘተ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት መተካት ነው፡፡ ለዚህ ብቁ የሆኑ ምሑራን ስላሉን ቁጭ ብለው ከሚያዩ ወይም የማያቋርጥ ሐተታ ከሚያበዙ፤ አዲሱን ሕገ መንግሥት አርቅቀው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ ቢያቀርቡ ይሻላል፡፡

  በተጨማሪም፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ አሰቃቂ ከሆነ የድህነት አረንቋ ለማዳን ተገቢ የሆኑ ምሑራን የተሟላ፤ ሥልታዊና ጥልቀት ያለው ብሔራዊ የልማት እቅድ አዘጋጅተው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያቀርቡ ያስፈልጋል፡፡

 2. ፈጣሪ አምላክ ይባርክዎ ግሩም ድንቅ የችግራችንን ምንሳኤ ቁልጭ አድርጎ ያሳየና መፍትሄውን ያመላከተ ጽሑፍ ነው ። ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በእውነት ወደ ትክክለኛ ለውጥ ፈላጊ ከሆነ እንደርስዎ ያሉ ምሁራን የሚሰጡትን ምክር መቀበልና ለመተግበር መነሳት አለበት ። በተለይም ዶክተር አብይ አህመድ የተግባር ቅደም ተከተል ፣ ቆራጥና ጥርት ያለ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ። የእሳት አደጋ ስራ በመስራትና በሺታውን ትቶ የበሺታውን ምልክት ለማስታገስ በመሯሯጥ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም ። ሌላው ጎጠኞቹ የሚያጮሁትን ጂራፍ ፈርተው የተሸሸጉ ምሁራን ችግሩ ከተፈጠረ ማምለጫ ባለመኖሩ እንደርስዎ በድፍረት የመፍትሄው አካል ቢሆኑ ይመረጣል ። እኔ የበፖለቲካ ድርጅቶች ነን ባዮች ስብስቦች ላይ ምንም እምነት ስለለሌኝ አንድነት ኃአይል የሆኑ ዜጎቻችን ትግሉ መሆን ያለበት በሕገመንግሥትና በጎሣ ፌደሬሺን ለውጥ ላይ መሆን አለበት ። የሚያስፈልገን የስርአት ለውጥ እንጂ የግለሰብ ወይንም የጎጥ አይደለም ። ዶክተር አብይ አሁን በያዙት ያልጠራ አቋም እንኳን ሊያሻግሩን እራሳቸውም አይሻገሩም ። ፖለቲካ የመምራትና የማስተዳደር ጥበብ እንጂ ቁማር አይደለም ። የወቅቱን ነባራዊ ችግር ለመፍታ በእውቀት የተካኑ ምሁራን ምክርና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል እንጂ አማካሪ ብለው በዙሪያቸው የኮለኮላቸው የ60ዎቹ በተንኮል የተመረዙ አዛውንት ማደናገሪያ አይደለም ።

  መስሚ ያለው ይስማ

  ፈጣሪ አገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.