Search
Close this search box.
Archives

The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles

English French German Hebrew Swedish Spanish Italian Arabic Dutch

ግልጽ ደብዳቤ ለሃይሌ ገብረሥላሴ (ከአበበ ገላው)

ውድ አትሌት ሃይሌ፣ ከነመላው ቤተሰብህ እንደምን ከርመሃል? ልጆቹ እንዴት ናቸው፣ አለምስ እንዴት ሰንብታለች?
ሰሞኑን የወዳጅ የዘመድ ምክር አላዳምጥ ብለህ እንደነ ጋሼ ግርማና ጋሼ ሃይለማርያም ደሳለኝ የህወሃቶች አሻንጉሊት መሆን እንዳማረህ ስሰማ በጣም ተገረምኩ። በመላው አለም ዝና ያተረፍክበትን እሩጫ ትተህ “ቤተመንግስት” ወይንም “ፓርላማ” ቁጭ ብለህ ዝንብ ማባረር ምን ይጠቅመኛል ብለህ ነው? አንተም እንደነጋሼ ግርማና ሀይለማሪያም በቁምህ ከመሞትህ በፊት ምክሬን ባትሰማ እንኳን ለማንኛውም ይቺን አጠር ያለች ጦማር ልጽፍልህ ወሰንኩ።
እኔ ያቺን “ሪከርድ” የሰበርክባትን ቲሸርት ነፍሳቸውን ይማርና ለዛ ህዝብ ላፈኑ፣ ላሰቃዩ፣ ለረገጡና ለጨረሱ፣ እንኳን በቁማቸው ሞተውም ላስመረሩን የሂትለርና የሞሶሊኒ ግልባጭ በአደባባይ ስትሸልም መካሪ ማጣትህን ገምቻለሁ። ግለሰቡ መሸለም ሳይሆን ተይዘው እንደ ናዚዎቹ ኑረንበርግ ለፍርድ መቅረብ ይገባቸው እንደነበር ጠፍቶህ ነበር ማለት አይቻለኝም። ግን ሃያሉ ፈጣሪ ፍርዱን እንደማያዘገይ አሳየን።
ከሁሉ የገረመኝ ደግሞ ልክ እንደ ህወሃት ካድሬዎች በኢቲቪ ቀርበህ “ታላቅ መሪ” አጣን እንባ አዋጡ እያልክ ካሜራ ፊት እንባ ስትጨምቅ ማየቴ ነበር። ያቺን የዋህ ደራርቱ “ለኛ ብሎ ታገለ፣ መስዋት ሆነ፣” ምናም እያለች ስታነባ በኢቲቪ ሳይ አንተ ሳታሳስታት እንዳልቀረህ በልቤ ገምትኩ። ከተሳሳትኩ ይቅርታ!
ውድ ሀይሌ፣ በህዝብ ዘንድ መከበርና መወደድ በቢሊዮን ዶላር እንኳን እንደማይገዛ ከቱጃሩ አላሙዲን መማር ይቻላል። ቱጃሩ አላሙዲን ሰሞኑን ወደ ዋሽንግተን ከአስር አመት በሁዋላ ሲመጡ የተከራዮት ታላቅ እስታዲየም በህዝብ ይጨናነቃል ብለው ጠብቀው ነበር። ይሁንና ነበር ባይሰበር ሆነና ነገሩ ያን ያሚያህል ስታዲየም እንኳን ሰው ወፍ ዝር ሳይልበት እንደሰማነው ከሆነ አራት ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰበት ድግስ ከንቱ ቀርቶ የሚበላው ጠፍቶ ተደፋ:: ቱጃሩም በሃፍረት ተሸማቀው መሰወራቸውን ስነግርህ በታላቅ ሃዘን ነው። ይህ ቱጃር በህዝብ ዘንድ ምን ያህል የተከበሩና የተወደዱ እንደነበር፣ የዛሬን አያድርገውና፣ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ሁሉ አልሳካ ቢላቸው ምስኪኑ ቱጃር ከሩቅ ሆነው አፋችንን ለማዘጋት እየዛቱ ነው። ዝርዝሩን ሰሞኑን አጫውትሃለሁ::
ቱጃሩ ድንገት በምርጫ 97 (ዝ)ንባቸውን በኩራት ደረታቸው ላይ ለጥፈው “ለህወሃት እሞታለሁ እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ” አበዙ። አስተዋዩ ህዝባችን ፊቱን አዞረባቸው። በቃ፣ ያሁሉ ቢሊዮን ከንቱ መሆኑ ታየ። ገንዘባቸውም አድናቂ አጣ፣ እርሳችውም ክብር እና ፍቅር በገንዘብ እንደማይሸመት ተረዱት። ዛሬ የሚያጅቧቸውም ጥቂት ግለሰቦች እርሳቸውን ሳይሆን ገንዘባቸውን ያፈቀሩ መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህ በክፉ ቀን ህዝብን ከከዳህ ቀባሪህ ጅብ እንጂ ሰው አይሆንም።

ወደ ተነሳሁበት ቁም ነገር ልመለስና ስለምኞትህ ትንሽ አስተያየት ልሰንዝር። ከሚድያ መረዳት እንደቻልነው ሁለት ምኞቶች አሉህ። አንደኛው የመቶ አለቃ ግርማን መቀመጫ መረከብ ሲሆን ሌላው ደግሞ የፓርላማ አባል ለመሆን ነው። እኔንም የገረመኝ የምኞቶችህ ከንቱነት ነው።
እንደምታውቀው “ፕሬዚዳንት” ተብሎ የሚሰየመው ሰው የህወሃቶች አሻንጉሊት ሆኖ ዋና ስራው እንግዶች መቀበልና መሸኘት ነው። ዶሮን ሲያታልሏት ሆነና ነገሩ አቶ መለስ ይህ “ስልጣን” የሚገባው ኦሮሞ ለሆነ ሰው ነው ብለው ባደባባይ ወስነው ስለነበር ቦታውን ሁለት የኦህዴድ አባላት ይዘውት ቆይተዋል። ኦህዴድ እንደሚታወቀው የፈጣሪው የህወሃት ሎሌ እንጂ ታላቁን የኦሮሞን ህዝብ ፈጽሞ አይወክልም። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን የጠየቁት እውነተኛ እኩልነት እንጂ አሻንጉሊት እንዳልሆነ እንኳን አዋቂ አፍ ያልፈታ ህጻን የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ነጋሶ የነበሩ ሲሆን እርሳቸውም አሻንጉሊትነት በቃኝ ብለው ጥያቄ መጠየቅ ሲጀምሩ እንዲነሱ ተደረገ። አንተ ጎበዙ እሯጭ በምን መስፈርት ነው ታዲያ ፕሬዚዳንት መሆን ያማረህ? የዘር መሰፈርትን ካላሟላህ፣ እጅና እግር እያለህ፣ ሕሊና ካለህ እንደ ኳስ መንከባለል እንዴት ይቻልሃል?
ነጋሶ ቢያንስ ከመሰናበታቸው በፊት መለስን “መንግስቱ መንግስቱን ሸተትከኝ” ማለታቸው የሰሩትን ስህተት ማረሚያ ሲሆናቸው ገነት ዘውዴን ግን ማስለቀሱን ተጽፎ አነበብን። እንደ ሰማነው ገነትን ያንሰቀሰቃቸው ላቶ መለስ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጥ ብቻ ሳይሆን የነጋሶን ወንበር ይመኙ ስለነበር ነው። “ፕሬዚዳንት ገነት ዘውዴ” ምናምን እያሉ እራስ ለማታለል ማለት ነው።
ነጋሶ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ስልጣን በሰላማዊ መንገድ በህዝብ ለተመረጠ ሰው ሲሰጥ በአይኔ በብረቷ አየሁ ብለው የድንቢጥ ማስክርነት ሰጥተው የነበሩት ገነት ዘውዴ፣ ለመለስ ምን አስለቀሳቸው ብለን መመራመር አያስፈልገንም። ነገሩ “ሆድ ሲውቅ…” እንደሚባለው መሆኑ ነው። ግን ያዞ እንባቸውም ከንቱ ቀረ። የወይዘሮ ገነት ዘውዴም ጌታ በዚያው አሸለቡ፣ እኛም ታዝበናቸው ቀረን። ምስኪን!
ነጋሶ ሲሰናበቱ ያተንኮለኛ አንባገነን ጥያቄ የማይጠይቅና አሻንጉሊትነቱን ሙሉ በሙሉ የሚቀበል ሰው አፈላልገው መቶ አለቃ ግርማን ፕሬዝዳንት ብለው ሰየሙ። ጋሽ ግርማ መቼም ድሮም ወስላታ እንደነብሩ አብረዋቸው የሰሩ ሁሉ የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። ህሊናቸው አይወቅሳቸውም። ይኸው እስካሁን አልጋ ላይ ሆነው፣ በዊል ቼይር እየተገፉ የህወሃቶች ላንቲካ እንደሆኑ መሞቻቸው ተቃርቧል። መቶ አለቃ ግርማ ወደ መቃብራቸው በህወሃቶች ሰረገላ ታጅበው ሲጋዙ ዶ/ር ነጋሶ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀው ለህዝባችን አንድነትና ነጻነት እየታገሉ ይገኛሉ። ከጥፋቱ የሚማር ሁሉ ታላቅ ሰው ነው።
ሃይሌ ሆይ፣ ያንተ ዋናው ጉብዝና እሩጫ ነው። እንኳን አጸያፊውንና የሚከረፋውን የህወሃቶች የዘር ፖለቲካ መፈትፈት ይቅርና ሽምግልናም አልሆነልህ። ታስታውስ እንደሁ አቶ መለስ በግፍ ያሰሯቸውን አገር ወዳዶች ለማስፈታት ከነፕሮፌሰር ኤፍሬም ጋር ሆነህ ያደረከው ጥረት መልካም ቢሆንም ምንም ያልበደሉ ንጽሃን ዜጎች ስንት ግፍና ጭፍጨፋ የፈጸሙትን መለስ ዜናዊን ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርጓል። ይሄ ደግሞ በታሪክ ያስወቅሳል።
በርግጥ ህወሃቶች ምን ቃል እንደገቡልህ አላውቅም። ይሁንና እንኳን ፕሬዚዳንትነት ጠቅላይ ሚኒስትነት ፈጽሞ አይመጥንህም። ጠቅላይ ሚኒስቴር ስል ጋሼ ሃይለማሪያም ትዝ አሉኝ። እኚህ ግለሰብ ገና አርባ ምንጭ ሲሰሩ ጀምሮ የሚታወቁበት አንድ መለያቸው ለህወሃቶ ጭራ መቁላት ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ባለራዩ መሪ ቢሮ ጠጋ ሲሉም ስራቸው ከጭራ መቁላት ወደ ምንጣፍ አንጣፊነት ከፍ እንዳለ የሚውቋቸው ሁሉ የሚናገሩት ጉዳይ ነው።
ዛሬ በህወህት ጄኔራሎችና አማካሪዎች ታጅበው የመሪነት ስልጣን ሳይሆን የአሻንጉሊትነት ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ። እኚህ ሰው የሌለና ያልነበረ ራእይ እጠብቃለሁ ብለው ደፋ ቀና ሲሉ በቁሙ የሞተው “መሪ” የሚል ቅጽል ወጥቶላቸው ተከብረው ሳይሆን የህወሃቶች ላንቲካና መጫውቻ ሆነው ሲሽከረከሩ ይውላሉ። ሰው ለህሊናው ማደርን ትቶ ሆድ ለመሙላት ብቻ ከኖረ የሚያዳምጠው ህሊናው የሚናገርውን እውነት ሳይሆን የሆዱን ፍላጎት ብቻ ነው። ጋሽ ሃይለማሪያም ህሊናቸውን አፍነው ሆዳቸውን እያዳመጡ መኖራቸው የሚያስከብራቸው ሳይሆን ለዘላለም የሚያስንቃቸው የታሪክ እውነታ ነው።
ውድ ሃይሌ፣ ሌላው ምኞትህ ደግሞ ፓርላማ ገብቶ ህግ ማውጣት ነው። ለመሆኑ ይሄ የህወሃቶች አዳራሽ ከመቼ ወዲህ ነው ለሃገርና ለወገን የሚጠቅም ስራ ሰርቶ የሚያውቀው። ወያኔዎች ዴሞክራሲ አመጣን ብለው ሁሉን ነገር ሙሉ በሙሉ እንደፈለጋቸው ተቆጣጥረው፣ ህዝብ እያስለቀሱ ፣ እያፈኑ፣ እየገደሉ፣ እያሰቃዩና እየዘረፉ ሲኖሩ ለመሆኑ መቼ ነው ፓርላማ ተብዬው የህዝብ ብሶት ተወያይቶ የሚያውቀው? የትኛውን መብት ነው ያስጠበቀው?የትኛውን ህግ ነው ያስከበረው? እኛ እስከምናውቀው ፓርላማ ማለት የህወሃቶች የቧልት አዳራሽ ነው። ቧልት ካማረህ፣ ለህወሃቶች ጭራ እየቆላህ፣ እያጨበጨብክ መኖር ካማረህ ወደ አዳርሹ ግባና የሚሉህን ሁሉ አድርግ። እኔ ግን ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደማታገኝ ከወዲሁ ልነግርህ እወዳለሁ።
እንደሰማሁት ከሆነ የሙስና እናት በመባል የሚታወቁት አዜብ መስፍን ከፓርላማ አባልነታቸው፣ ከኤፈርት ቁንጮነታቸው በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከንቲባና የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መሆን ይፈልጋሉ። አዜብ ከባላቸው ሞት በሁዋላ ፍላጎታቸውም በጣም እንደጨመረ እንደውም የመለስን እራእይ አስጠባቂ እኔ ነኝ ማለታቸው ትክክል ነው። በዘር ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ደም እየመጠጠ ያለው ኤፈርት ባለቤቶ ጋር መወዳደር በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በንግዱም ዘርፍ ብዙ ኪሳራ ስለሚያስከትልብህ ጠንቀቅ ብትል ይሻልሃል። ፕሬዚዳንትነቱንም ሆነ ፓርላማውን ለነአዜብ ተውላቸው። የነሱ የፍርድ ቀን እሩቅ አይደለም…
አንተም የኢትዮጵያን ህዝብ ማገልገል ከፈለክ ህዝባችን ከህወሃቶች የአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል በሙሉ ልብህ ደግፍ። ትንሽም ብትሆን መሰዋእትነትና ዋጋ ክፈል። ፓርላማም ሆነ ቤተምንግስት ገብተህ የህወሃቶች ጉልቻ አትሁን።
ለማንኛውም የኔን ምክር ተውና የባለቤትህን የአለምዬን ምክር ስማ። ሴት መቼም ሁል ጊዜም ብልህ ነችና፣ አለም አያዋጣህም ብልሃለች። “ጨው ለራስህ ብትል…” ነው ነገሩ።
እኔ በበኩሌ የምመኘው በአገሬ እንደማንም ተራ ዜጋ ተከብሬ የነጻነት አየር እየተነፈስኩ መኖር ብቻ ነው። ከቤተ መንግስት ይልቅ የእናቴ ደሳሳ ጎጆ ትናፍቀኛለች።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top