Dark
Light
Today: December 25, 2024

Mothers Day Special: የእናቶችን ሞት ለመቀነስ…

May 9, 2012

ከአልማዝ አያሌው

ለሰው ልጆች ወልዶ እንደመሳም የሚያስደስት ነገር የለም። እንኳን በራሱ የወለደውን ሌሎች ሊስሙለት እንኳን ደስታቸው እጥፍ ነው። በተለይ ለእናቶች ለዘጠኝ ወራት የተጨነቁበትን፣ በምጥ ወቅት መከራ ያዩበትን ልጅ አሳድገው ለቁም ነገር ከማብቃት በላይ ምኞት የላቸውም። ያሰቡት ሲሞላ ደግሞ በህይወታቸው ሙሉ ደስተኛ ይሆናሉ። በተለይ በልጅነት የዕድሜ ዘመናቸው። ከነተረቱስ «የወለዱትን ሲስሙለት…» ይባል የለ። ይሁን እንጂ ወላጆችን ዘመድ አዝማድና ጐረቤትን የሚያሳቅቅና የሚያሳዝን የልጆች ሞት በየአጋጣሚው ይከሰታል። በተለይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን ሞት ያጠቃቸዋል።
ከዚህም ጐን ለጐን የወለዷቸውን ልጆቻቸውን ማሳደግ ሳይችሉ ቤተሰባቸውን በትነው ከዚህ ዓለም የሚለዩ እናቶች ቁጥርም ቀላል አይደለም። ይህ ሁኔታ ዓለምን ያስጨነቀ፣ ሃገራትን ያሳሰበም ሆኖ ከርሟል። ሰሞኑን ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የ2003 የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት ውጤት ግን በተለይ በሕፃናት ሞት መቀነስ እና በቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ የምስራችን የሰነቀ ዜና አብስሯል። በእናቶች ሞት ዙሪያ ደግሞ አሁንም የበለጠ ሥራ መሠራት እንዳለበት የሚጠቁም ጭምር።
ይሄ ጥናት የሚያመለክተው በተለይ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ልጆች ሞት ባለፉት አስር ዓመታት መቀነሱ ነው። የማዕከላዊ ስታትቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳሚያ ዘካሪያ ያሉትም በ1992 ዓ.ም. አካባቢ በህይወት ከሚወለዱት አንድ ሺህ ሕፃናት መካከል በህይወት የመቆየት ዕድል የሚገጥማቸው 834 ብቻ ናቸው። ቀሪዎቹ 166 ሕፃናት እጣ ፈንታ ግን ይህቺን ዓለም ሳይኖሩባት መሰናበት ነው።
ይህ ሁኔታ ዓለማትንና ሃገራትን አነጋግሯል። አሳስቧልም ለመፍትሄም ግራቀኝ እንዲቃኙ ጋብዟል። የሕፃናት ሞት የሚቀንስበትን መላም ለመፈለግ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ መፍትሄ ያሏቸውን ጠቁመዋል። የሕፃናት የበሽታ መከላከያ ክትባት፣ አመጋገብ፣ የጤና አጠባበቅ ብቻ ሕፃናትን በጤንነት ለመቆየት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የማሟላቱና የመሥራቱ ሁኔታ ለሁሉም አገራት ትልቅ የቤት ሥራ ሆኗል።
በተሠራው የቤት ሥራ ታዲያ ለውጥ አልመጣም ማለት አይደለም። መጠነኛም ቢሆን በኢትዮጵያ ለውጦች ነበሩ። በ1992 ዓ.ም ከታየው በተሻለ በ1997 ዓ.ም. በህይወት ከተወለዱ አንድ ሺ ሕፃናት መካከል ከዚች ዓለም በሞት የተለዩት ወደ 123 ዝቅ ብሏል። እንዲሁም በ2003 በተካሄደው የሥነ ህዝብና ጤና ጥናት ደግሞ የሞቱ መጠን ወደ 88 ዝቅ ብሏል። ወይዘሮ ሳሚያም በአሁኑ ወቅት ከ11 የኢትዮጵያ ልጆች መካከል አንድ ሕፃን ዕድሜው 5 ዓመት ሳይሞላው ይሞታል። ይህም ከዚህ በፊት ከነበረው የሕፃናት ሞት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ መቀነስ አሳይቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የአመጋገብ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱ በጥናቱ ተመልክቷል። ይኸውም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት ልጆች መካከል በ1992 ዓ.ም 58 በመቶ የነበረው የቀነጨሩ (ቁመታቸው ከዕድሜያቸው ጋር ሲነፃፀር በጣም አጭር የሆኑ) ልጆች ቁጥር በ2003 ዓ.ም ወደ 44 በመቶ ቀንሷል። ክብደታቸው ከዕድሜያቸው ጋር ሲነፃፀር በጣም ቀጭን የሆኑ ልጆች ብዛትም በ1992 ከነበረው 41 በ መቶ ወደ 29 በመቶ መቀነሱ ተነግሯል።
በቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ ከፍተኛ መሻሻል እንደታየ ይናገራሉ ዋና ዳይሬክተሯ። በቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተደርጐ ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥ መታየቱንም ይገልጻሉ። «ከአስር ዓመት በፊት የዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ተጠቃሚ ቁጥር አራት በመቶ ብቻ የነበረው አሁን ወደ 27 በመቶ ደርሷል» ይላሉ ያለውን መሻሻል ሲገልጹ።
ለቤተሰብ ዕቅድ ዋናው መሻሻል ምክንያት በመንግሥት በኩል ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ። በተለይ በጤና ኤክቴንሽን ፕሮግራም ባለሙያዎች አማካይነት ሴቶች ስለቤተስ ምጣኔ በቂ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉ፣ ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ ዘዴዎች መጠቀሚያዎችን ማዳረስ፣ ሴቶችን በማብቃት ዙሪያ ሰፊ ሥራ መሠራቱ ለውጤቱ ጉልህ ሚና መጫወቱን ነው የተናገሩት። በ1997 ዓ.ም ዘመናዊ የወሊድ መከላከያ ዘዴ ይጠቀሙ ከነበሩት እና በወቅቱ በጋብቻ ላይ ከነበሩ 14 በመቶ ሴቶች አሁን በእጥፍ ከፍ ማለቱን ወይዘሮ ሳሚያ ይናገራሉ። «በኢትዮጵያ በአማካይ የአንዲት ሴት የወሊድ መጠን በ1997 ዓ.ም. ከነበረው አምስት ነጥብ አራት ልጆች በ2003 ዓ.ም ወደ አራት ነጥብ ስምንት ልጆች ቀንሷል» ብለዋል።
ወይዘሮ ሳሚያ እንዳሉት በ2003 በተካሄደው የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት ውጤት መሠረት መሻሻሎች የታዩባቸው የሕፃናት እና ልጆች ሞት፣ የቤተሰብ ዕቅድ፣ የቤተሰብ የትምህርት ሁኔታ፣ ሴቶችን የማብቃት ሥራዎች ናቸው። መሻሻል ያልታ የበት ደግሞ የእናቶችን ሞት መቀነስ ላይ ነው።
«በ2003 የተካሄደው የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት አጠቃላይ ሁኔታ ሲገመ ገም እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ጥናቱ ሲካሄድም ሁሉንም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ባዳረሰ እና ወካይ በሆነ ሁኔታ ነው» በማለት ከዚህ ቀደም ከተ ካሄዱት ጥናቶች የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ። አርብቶ አደሩን አካባቢ ሙሉ በሙሉ የሚወክል ሲሆን፤ በአፋር ክልል የሚገኙትን አምስት ዞኖች እንዲሁም በሱማሌ ክልል ደግሞ ካሉት ዘጠኝ ዞኖች ስድስቱን ያካተተ እና የአርብቶ አደሩን አኗኗር የሚያሳይ ጥናት እንደነበር አስረ ድተዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱም የጥናቱ ውጤት መን ግሥት ያስቀመጣቸውን ግብ እና የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉ ይገልጹታል። «በጥሩ ደረጃ ላይ የምንገኝ መሆኑን አመላካች
ውጤት ነው። በመ ሆኑም ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሳችንን የምና በስርበት ነው» ብለዋል።
ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ያሳካሉ ከሚባሉት ሀገሮች ኢት ዮጵያ አንዷ ናት። በጤና አንፃር የሕፃትን ሞት መቀነስ አንዱ ሲሆን፤ በምዕተ ዓመቱ ግብ ከሚወለዱ አንድ ሺ ሕፃናት የሚሞቱትን ሕፃናት ቁጥር ወደ 68 ማውረድ መሆኑን ይና ገራሉ። አሁን ባለው ፍጥነት ኢትዮጵያ ከም ዕተ ዓመቱ ግብ የጊዜ ገደብ ቀድማ ታሳካዋለች ብለዋል።
ሌላው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ኤች አይ ቪ፣ ወባና ቲቢን መቆጣጠር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በእ ነዚህም ዙሪያ አበረታች ውጤቶች መገኘ ታቸው ይፋ አድርገዋል። በ2003 በተደረገው የሥነ ሕዝብ እና ጤና ጥናት ውጤት መሠረት ባይሆንም በሌሎች በተደረጉ ጥናቶች የኤች አይ ቪ ሥርጭት መቀነሱንና የሕዝቡ ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን አመላካች ውጤቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። በወባ በሽታ እና በወባ ምክንያት የሚመጣ በሽታም እንዲሁም ቲቢ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ይገልጻሉ።
ሚኒስትር ዴኤታው የተገኙት ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ቢገልጹም ለቀጣዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም። በተለይ የእናቶች ሞት አለመቀነሱ ወደፊት ከፍተኛ እና የተጠናከረ ሥራ መሥራትን የሚያስገድድ መሆኑን አመላ ክተዋል።
«በጥናቱ ውጤት መሠረት ለውጥ ያልታየው በእናቶች ሞት ላይ ነው። ይሄም መንግሥት ካስቀመጠው እና ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ አንፃር ዝቅተኛ አፈፃፀም አሳይቷል። ይሄ ደግሞ በተለይ የእናቶችን ሞት ከመቀነስ አንፃር ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳያል» በማለት የእናቶች ሞት አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
በጥናቱ መሠረት አሁን በጤና ተቋማት የሚወልዱ ሴቶች ቁጥር አስር ከመቶ ሲሆኑ በ1997 ዓ.ም ከነበረው የአራት በመቶ ብልጫ አለው። ከአስር ሴቶች መካከል ስድስቱ በጤና ተቋማት መውለድ አስፈላጊ አይደለም ብለው የሚያምኑ ሲሆን፤ 30 በመቶ ያህሉ ደግሞ ከባህልና ከእምነት ጋር በተያያዘ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የማይፈልጉ ናቸው። ዶክተር ከሰተብርሃን እንዳሉትም አስር በመቶ ብቻ እናቶች ለወሊድ ጊዜ የጤና ተቋማትን በመጐብኘታቸው የእናቶችን ሞት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ አልተቻለም።
እናቶች ወደ ጤና ተቋማት የማይሄዱበት ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆንም የትራንስፖርት አለመኖርና የአገልግሎት ክፍያ መኖር ተጠቃሽ መሆናቸውን ዶክተር ከሰተብርሃን ይገልጻሉ።
በቀጣይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ያም ናሉ። በተለይ በጤና ኤክስቴንሽን ከሕዝቡ የጤና ሠራዊት በመፍጠር ሴቶች እርስ በእርስ የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደ ሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ።
እናቶች የጤና ተቋማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ለማስተካከል ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት የማመቻቸት ሥራ እየተ ሠራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤ ታው ይናገራሉ። እያን ዳንዱ የክልል ወረዳ አንድ አምቡላንስ በማግ ኘት እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት በቀላሉ እንዲ ደርሱ ይደረጋል። «እናቶች በትራ ንስፖርት ረገድ የሚገ ጥማቸውን ችግር ለማቃለል 800 አምቡ ላንሶችን ለየክልሎች የማከፋፈል ዕቅድ አለ። በዚሁ መሠረት በቅርቡ 310 አምቡ ላንሶችን ለክልሎች ይሰጣል። ቀደም ሲል 50 አምቡላንሶች ተሰጥተዋል» በማለት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እየተሠራ ያለውን ሥራ ይጠቅሳሉ።
የእናቶችን ሞት መቀነስ እንደ ሌሎች ሥራ ዎች ኅብረተሰቡ ላይ ማተኮር ብቻ በቂ እንደ ማይሆን ነው የተናገሩት። «ጠንካራ የጤና ተቋም፣ ጠንካራ ሪፈራል ስርዓት፣ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እስከ ገጠር ድረስ ማዳረስ ያስፈልጋል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታም ጤና ተቋማትን በሰፊው መሥራት ተችሏል። በሕክምና መሣሪያዎች ተደራጅተዋል። ይሁን እንጂ የመድኃኒት እጥረቶች አሉባቸው» በማለት የተሠሩትን ሥራዎች ይናገራሉ። የመድኃኒት እጥረቱም የተከሰተው አብዛኛው የገጠር ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡት በነፃ ስለሆነ ከተገልጋይ በሚሰበስቡት ገንዘብ መልሰው መግዛት እና አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው መሆኑን ያብራራሉ።
እነዚህን ችግሮች በየደረጃቸው ለማስወገድ መንግሥት የጤና ኢንሹራንስ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ያስታ ውቃሉ። በገጠር የሚኖሩትም «ኮሚዩኒቲ ቤዝድ ኤንድ ኢንሹራንስ» ለመተግበር ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ይገለጻሉ። በአሁኑ ወቅትም በ13 ወረዳዎች ላይ የሙከራ ትግበራ መጀመሩን ነው የገለጹት። በዚህ መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ በሚታመምበት ጊዜ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ነፃ አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል። «ኢንሹራንሱን የከፈለ ኅብረተሰብ ነፃ ሕክምና እና መድኃኒት የሚያገኝበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። ከዚህም ጐን ለጐን ከመንግሥት እና ከአጋር ድርጅቶች በጣም ወሳኝ የሚባሉ መድኃኒቶችን የማቅረብ ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው» በማለት ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን ጠቁመውናል።
የ2003 የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት ውጤት በአንድ መልኩ አስደሳች በሌላ መልኩ ደግሞ የማንቂያ ደወል ነው። በመሆኑም ደወል በተሰማባቸው አቅጣጫዎች በተለይም የእናቶችን ሞት በመቀነሱ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሰንቆ መሥራት ያሻል። በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከተው ሁሉ የሩጫ ፍጥነቱን ማሻሻል ዛሬውኑ መጀመር ይኖርበታል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

World TB Day – Saturday, March 24, 2012

Next Story

Not allowed to move for FIVE months: Themum who had to lie in bed 24 hours a day or risk losing her babies

Latest from Blog

A demon by the Bank of the Blue Nile River

By Aschalew kebede Abebe The Triangular Entanglement It had been more than a century since the foundation of the conspiracy theory had lain down. It had begun when Theodore Herzl proposed to
Go toTop